Fana: At a Speed of Life!

የ11 ልጆች አባትና የ69 ዓመቱ አዛውንት የዘንድሮ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪ ሆነዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ11 ልጆች አባት እና የ69 ዓመቱ አዛውንት ታደሰ ጊችሌ የጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተቀበላቸው ካሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስደው 502 የመግቢያ ነጥብ ያመጡት እና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት ተማሪ ታደሰ ጊችሌ ፥ ከምዕራብ ወለጋ ገንጅ ወረዳ መነሻቸውን አድርገው ለትምህርት ጅማ ዩኒቨርሲቲ በዕድሜ ከልጆቻቸው በትምህርት ደግሞ ከእኩዮቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል።

በ1945 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ታደሰ የ11 ልጆች አባት ሲሆኑ ፥ ባለቤታቸው ወይዘሮ ቢዲጡ ቶላ እና ልጆቻቸው ‘’ትምህርቴን ጨርሼ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ትናንትም ዛሬም አስተዋፅኦ አድርገዋል’’ ብለዋል።

እንደ እኩዮቻቸው ፊደል ቆጥረው ሳይንሱን አርቅቀው የሚፈልጉበት የልጅነት ራዕያቸዉ ላይ ለመድረስ በቤተሰብ ሃላፊነትና በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ቢፈተኑም ፥ ካሰቡበት ለመድረስ ባላቸው ጠንካራ የመማር ፍላጎት ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ ገቢ የሆኑት ተማሪ ታደሰ ፥ ‘’አንዳንዶች በዚህ እድሜህ ትምህርቱን አቋርጠህ ለምን ወደ እርሻህ አትመለስም ይሉኛል ፤ እኔ ግን የልጅነት ህልሜን ማሳካት ስላለብኝ ከትምህርቴ ጎን ለጎን የእርሻና የቡና ችግኝ እያስፋፋሁ ቆይቻለሁ’’ ብለዋል።

ተማሪ ታደሰ ጊችሌ ወደ ፊት በዩኒቨርሲቲ ቆይታ በጤና ዶክትሬት ማጥናት እና በሕክምናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ኢትዮጵያን እና ወገኔን ማገልገል እፈልጋለሁ ማለታቸውን ከጅማ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.