Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ስልጠና ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት በሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት የሚሰጠውን የአንድ ቀን ስልጠና ዛሬ ጠዋት አስጀምረዋል።

በዚህ ወቅትም ቡድኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት በኩል በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን በማስታወስ በዚሁ ስራ የሚሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራን ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ለማከናወን መሰል ስልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም ስራውን በአግባቡ እና በተደራጀ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል በስራው ተሳታፊ የሆኑ አካላት የዘርፉን ጽንሰ ሃሳብ እና በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሙያው በቂ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ምሁራን ስልጠናው እንዲሰጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስልጠናው በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕለማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል እና በውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ኢኒስቲቲዩት በጋራ የተዘጋጀ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ስልጠናው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የድንበር ተሻጋሪ ሃብቶችና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ በምትከተለው አቅጣጫ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምንነት እና ጠቀሜታው፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በሀገሪቱ የሚገኙ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የምርምር ተቀማት ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት በለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን በማካተት የተቋቋመ ነው።

ቡድኑ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በግብጽ፣ በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በኡጋንዳ እንዲሁም በቅርቡ በኤርትራ በመንቀሳቀስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር እና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የመገንባት ስራ እየሰራ ይገኛል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.