Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ ቆይተዋል ያላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች በ72 ሰዓታት ከሀገር እንዲወጡ አዘዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአትዮጵያ የዓለም ህጻናት አድን ድርጅት ጽህፈት ቤት (ዩኒሴፍ) እና በተመድ የሰብዓዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነት ሲሠሩ የነበሩ እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ የውጭ ሃገር ዜጎች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ መታዘዙን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከዩኒሴፍ ተወካይ በተጨማሪ ከሀገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ግለሰቦች፥ በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ እየሠሩ ያሉ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት ከሀገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ከተሰጠባቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል ሚስ አደል ኮድር በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ ከዩኒሴፍ ሃላፊዋ በተጨማሪ፥ ከሀገር ውስጥ እንዲወጡ ከተወሰነባቸው ግለሰቦች መካከል በኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ምክትል አስተባባሪ የሆኑት ሚስ ጋዳ አል ጣሂር ሙዳዊ ይገኙበታል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ አገልግሎት አስተባባሪና ቋሚ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የሰላምና ልማት አስተባባሪ የሆኑት ሚስተር ኪዌሲ ሳንስክሎቴ እንዳሉበት ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ሚስተር ሳኢድ ሞሐሙድ ሔርሲ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ኃላፊ እንዲሁም ሚስተር ግራንት ሊቴ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ አገልግሎት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሰብዓዊ ድጋፍ ምክትል አስተባባሪ ተጠቅሰዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ባልደረባ ሶኒ ኦኒግ ቡላ እንዲሁም የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ ሚስ ማርሲ ቪጎዳ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ÷ ከድርጅቶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማጤን እንደሚገደድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.