Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን እንዳሰፋው ሁሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል- አቶ ታዬ ደንደአ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት መጪው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ተአማኒነት ያለው እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራው ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል አሉ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ፡፡
አቶ ታዬ ደንደአ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግስት በማህበራዊ ሚዲያ ባሰባሰበው ህዝባዊ ሀሳብ ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኃላፊው በሰጡት ማብራሪያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በሰራው ስራ ከውጪ ሀገር ጭምር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
የመደራጀት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መከበሩን አንስተው አፋኝ የነበሩ የህግ ማዕቀፎችም ማሻሻያ እንዲደረግባቸው መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የሚዲያ ነፃነትን ለማስከበር ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው ህግና ስርዓትን ጠብቆ መጫወት የባለቤቱ ድርሻ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ፖለቲካን አሳብበው አለመረጋጋት፣ እልቂትና ግጭትን መቀስቀስ ግን በህግ ያስጠይቃል ነው ያሉት ኃላፊው፡፡
ጉዳያቸው በህግ እየታየ ስላለ የፖለቲካ ሰዎች ጥያቄ ተነቶላቸው ህግ የያዘውን ህግ ይፈታዋል ሲሉ መልሰዋል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ሲያሰፋ ብዙ ታግሷል፤ ህግና ስርዓት ሲጣስ ደግሞ የህግ የበላይነትን ማስከበር ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦች መብታቸውና አንድነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
መንግስት የኦሮሞ ህዝብ እና የሀገሪቷን ህዝቦች አንድነትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራው ሁሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም የድርሻቸውን መጫወት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ ግልፅ እና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ እኛ በቁርጠኝነት እንሰራለን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲሁ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ታዬ ደንደአ ከኦነግ ሸኔ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ኦሮሞ ድጋፍ ፈልጎ ሲማቅቅ እና ባዶ እጁን ሲታገል አንድም ጥይት ያልተኮሰ ቡድን ከለውጡ በኋላ ትግል ለምን ታየው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ኦነግ ሸኔ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገል መንግስት በትዕግስት ረዥም ርቀት ቢጓዝም ቡድኑ በእምቢ ባይነቱ በመቀጠል አመራር በመግደል፣ ንብረት በመዝረፍ እና የህዝቡን ሰላም በማናጋት ሀገር የሚያሸብር ሆኗል ብለዋል፡፡
ጠላት ላይ አንድም ቀን ሳይተኩስ የቆየው ሸኔ አሁን ላይ ጫካ ጫካ የሚለው በኦሮሚያ እና በሀገር ደረጃ የቀጠለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ብቻ ነው ይላሉ አቶ ታዬ፡፡
መንግስት በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑን በመግለፅ ቡድኑን በተመለከተም እምቢ ባይነቱ በህግ የበላይነት የማስከበር ስራ ይፀዳል ብለዋል፡፡
ሸኔ ከኦሮሚያ ሲፀዳ ክልሉ ሰላም ይሆናልም ነው ያሉት አቶ ታዬ ደንደአ፡፡
የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲሁ የበኩላቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲ እና እኩልነት ሲረጋገጥ የኦሮሞም ሆነ የሌላው ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ያገኛል፤ ስለዚህ ሁሉም በሰላማዊ መንገድ ሊታገል ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሙስናን በማጋለጥ ህዝቡ መንግስትን ሊደግፍ ይገባዋል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደሚታትረው ሁሉ የግል ባለሀብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በልማት ላይ ማፍሰስ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ህዝቡም ቢሆን ከሚያገኘው ገቢ በማስቀመጥ ቁጠባን ባህሉ ሊያደርግ ይገባዋል ይላሉ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ ከተጠየቁ ጥያቄዎች መሀል አንዱ የህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሲሆን አቶ ታዬ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ የሚያጣላ እንዳልሆነ እና አስፈላጊ መሆኑ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሲታመንበት በጥናት ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ለስራ ዕድል ፈጠራ የ5 የሚውል ቢሊየን ብር በተዘዋዋሪ ፈንድ መለቀቁን አስታውሰው ፈንዱን የወሰዱ አንዳንዶች ሰርተው ተለውጠውበት ከመመለስ ለመሰወር ሲሞክሩ ይታያሉ ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡
የሰላም እጦት ካለ ለኢንቨስትመንት ፍሰት አስቸጋሪ መሆኑን አንስተው ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማስመዝገብ ላይ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው በየአረብ ሀገራቱ የሚቸገሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መንግስት በዜግነት ዲፕሎማሲ ሰፊ እና ተጨባጭ ስራ መስራቱን አንስተው የደላላን ሰንሰለት መቁረጥ ደግሞ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የኦሮሞ ህዝብ በሀገር ግንባታ፣ ጠላትን በመመከት እና አንድነትን በማስጠበቅ ሰፊ ድርሻ ያለው መሆኑን አስታውሰው ኢትዮጵያ ለኦሮሞም ከሌሎች ህዝቦች እኩል ሀገሩ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.