Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 68 ሽጉጦችና ከ2 ሺህ በላይ የክላሽን ኮቭ ጥይቶች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሠሩት የተቀናጀ ሥራ በተሽከርካሪ አካል በድብቅ በተዘጋጀ ስፍራ ተጭነው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡ 68 ሽጉጦች እና ከ2ሺህ በላይ የክላሽን ኮቭ ጥይቶች መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ህዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰፈረ ሰላም አካባቢ ከሚገኘው የገበያ ማዕከል 2 ሺህ 475 የክላሽን ኮቭ ጥይቶች መያዛቸውን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
ከወትሮው በተለየ መልኩ ከሚሸጡ የተለያየ አይነት ጨርቃ ጨርቆች ጋር በሲሚንቶ ወረቀት ተጠቅልለው በማዳበሪያ ተቋጥሮ በሰው ሸክም ሲንቀሳቀስ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ሊያዙ ችለዋል ነው ያለው ፖሊስ፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ ህዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፅዮን ሆቴል አካባቢ መነሻውን ከባህር ዳር ባደረገ ተሽከርካሪ የኋላ ፍሬቻ መብራቱ ተነቅሎ በተሽከርካሪው አካል በድብቅ በተዘጋጀ ስፍራ (ሻግ) ተጭነው ወደ አዲስ አበባ የገቡ 68 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ተይዘዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም 1 ተጠርጣሪ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሽብርተኛው ህወሓትን ተልዕኮ የተቀበሉ ተላላኪዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚያደርጉትን ህገ-ወጥ ተግባር በማክሸፍ ረገድ ህብረተሰቡ ለፀጥታ ኃይሉ የሚያደርገው ተባባሪነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.