Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 100 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሞተር አልባ ትራንስፖርት መስመር ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚቀጥሉት 10 አመታት መቶ ኪሎሜትር የሚሸፍን የሞተር አልባ ትራንስፖርት መስመር ሊዘረጋ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ቢሮ በከተማዋ በአዲስ መልክ ሊተገበር የታሰበውን የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የሞተር አልባ ትራንስፖርት እንደ አዲስ አበባ ላሉ ከተሞች በኢኮኖሚ፣ በጤና እንዲሁም ከምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ አንጻር ያለውን ጠቀሜታ በማስመልከት ገለጻ ተደርጓል።

እንዲሁም አገልግሎቱ በምን አይነት አካሄድ ሊተገበር ይችላል በሚሉት ሐሳቦች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ፕሮጀክቶች በአስፈጻሚ አካል ማጣትና በአተገባበር ችግር ባለመሳካቱ ችግሩን ለመቅረፍ በትራፊክ ማኔጅመንት ቢሮ በኩል እራሱን የቻለ አንድ የስራ ክፍል መቋቋሙ ተነግሯል፡፡

ሲደርሱ የነበሩትን የአደጋ ስጋቶች፣ ስርቆትና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮችን ለመቅርፍ አዲስ የተቋቋመው የስራ ክፍል ትልቅ ሚና አንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰመረ ጅላሉ ÷በቀጣዮቹ 10 አመታት በከተማዋ መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ይዘረጋል ብለዋል፡፡

የፊታችን እሁድ ወደ ስራ አንደሚገባ የተነገረው ከጀሞ እስከ ለቡ ያለው የብስክሌት ሞተር አልባ ትራንስፖርት መስመር አገልግሎቱ በአዲስ መልክ ከሚጀመርባቸው መንገዶች አንዱ ሲሆን በአስር አመት ውስጥ ሊተገበር ከታሰበው የ100 ኪሎሜትር እቅድ አካል መሆኑንም ሃላፊው አብራርተዋል፡፡

መንገዱ የተመረጠው በአካባቢው በተከታታይ ‹‹እንደመንገድ ለሰው› ያሉ ከመኪና ነጻ ሁነቶች የተከናወኑበት፣ የብስክሌት ትራንስፖርት በብዛት ስለሚገኙበትና በአካባቢዎቹ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ከለቡ እስከ ጀሞ ካለው መስመር በተጨማሪ ከቱሉ ዲምቱ-ቃሊቲ፣ ከሃይሌ ጋርመንት-ጀሞ በቅርቡ የሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚጀመርባቸው የከተማዋ ክፍሎች መካከል ናቸው፡፡

ረጅም ርቀት የሚታጠር የህንጻ ዲዛይን እንዳይኖር እና በየመሃሉ የሞተር አልባ አቋራጭ መንገዶች እንዲሰሩ ለማድረግ መታሰቡንም ነው የተነገረው።

ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካካል 54 በመቶው እግረኛ፣ 31 በመቶው የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ የቀሩት 15 በመቶዎቹ ደግሞ የቤት መኪና ተጠቃሚዎች መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.