Fana: At a Speed of Life!

በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ገለጸ፡፡
 
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡልቱማ ቂጣታ÷ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የሃገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
በአጠቃላይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 16 ሺህ 402 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ስርቆት መፈጸሙን ጠቁመው፥ በዚህም 26 ሚሊየን 94 ሺህ 75 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
 
አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በልደታ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑን የገለፁት አቶ ቡልቱማ÷ በዚህ ሳምንት ብቻ መሪ ሎቄ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ፣ ልደታ እና ሳሪስ አቦ አካባቢ ከመሬት በታች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ ስርቆት እና ውድመት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
 
ተቋሙ እየተባባሰ የመጣውን የባቡር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት ለመከላከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ድርጊቱን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ነው የተናገሩት።
 
 
እኩይ ተግባሩን ለመከላከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት በመስጠት ተገቢ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግና ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው÷ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀምን የስርቆት ድርጊት ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በስራ ላይ ቢውሉም በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣና ከፍተኛ የሃገር ሃብት እየተዘረፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በሃገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል ብለዋል፡፡
 
በ2014 በጀት ዓመት 11 ወራት በተደረገ ክትትልና የማጣራት ስራ በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በቁጥር ከ37 በላይ ‘’የስርቆትና ጉዳት ማድረስ’’ የወንጀል ተግባራት ተፈፅመው ለተለያዩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ክስ ተመስርቶ በምርመራና በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።
 
በመሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀም የስርቆት ተግባር ለሃገር፣ ለተቋምና ለማህበረሰብ ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን እንደራሱ ንብረት አድርጎ ሊጠብቅና ይህን መሰል እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ሲመለከት በተቋሙ 905 ነጻ የጥሪ ማዕከል ጥቆማ ሊሰጥ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ሊያሳውቅ ይገባል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.