Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጥያቄያችን ይመለስልን የሚሉ ሰልፎች ተካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጥያቄያችን ይመለስልን የሚሉ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ሰልፎቹ የክልሉ መንግስትን ምላሽ የሚፈልጉ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነገቡ መሆናቸውን በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በሽሬ እንደስላሴ እና አካበቢው እንዲሁም በዋጅራት አካባቢ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የመሰረተ ልማት እንዲሁም ከስራ ዕድል ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።

በተለይም በሽረ እንደስላሴ አካበቢ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በወረዳ የመደራጀትና የወረዳ ዋና ከተማ ከመሆን ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ቢነሱም የክልሉ መንግስት አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ብለዋል።

በክልሉ እስከታች ቀበሌ ድረስ ስልጣን በኔትዎርክ ትስስር የሚሰጥ እንደሆነና ህዝቡን የሚጠቅሙ ስራዎችም እየተሰሩ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ለዓመታት ሲነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችም አሁንም ድረስ አለመመለሳቸውን፤ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ ወጣቶችም የስራ ዕድል ጥያቄ ቢያነሱም ያን የመመለስ ፍላጎት በክልሉ መንግስት ዘንድ አለመኖሩን ተናግረዋል።

በተለይም በሽረ እንደስላሴ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤት ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥም እስካሁን ወደ ግንባታ አለመገባቱን ነዋሪዎቹ አንስተዋል፤

ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ባገኘነው መረጃ መሰረትም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚውል 20 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገቢ ተደርጓል።

ግንባታው በክልሉ መንግስት መካሄድ ቢኖርበትም እስካሁን ግንባታው አለመከናወኑንም የከተማው ነዋሪዎች ነግረውናል።

ወጣቶች መሰል የስራ ዕድል ጥያቄዎችና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ሲያነሱም ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የትግራይን አንድነት ከማይፈልጉ እና ከትግራይ ጠላቶች ጋር እየሰራችሁ ነው፤ ባንዳ ናችሁና ሌሎች ፍረጃዎች እንዳሉም በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉ አካላት ተናግረዋል።

ሰልፎቹ በሰላማዊ መልኩ መካሄዳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ በክልሉ መንግስት ዘንድ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የማስፈራራት አዝማሚያ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ነዋሪዎቹ ለሚያነሷቸው ረጅም ዓመታት ለፈጁ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጠን ከሆነም የፌዴራል መንግስት ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደመሆናችን ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ያሰጥልን ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ስለተካሄዱት ሰልፎችም ሆነ እየተነሱ ስላሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጠን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በስልክ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

ከዚህ በኋላም በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.