Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው

አዲስ አበባ ፣ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጤናማ ያልሆነ የአናኗር ዘይቤ በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ማድረጉ ተገለጸ።
ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር ሕመም፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካል ችግር፣ ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ የደም ስር ችግሮችና የመሳሰሉት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በእነዚህና መሰል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ በዓለም ላይ በየዓመቱ 41 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ደግሞ 15 ሚሊየን የሚሆኑት ዕድሜያቸው በ30 እና 69 ዓመት መካከል የሚገኙ መሆኑን መረጃው ያሳያል።
በዓለም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚመዘገበው ሞት 85 በመቶ የሚሆነው እየተከሰተ ያለው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የስኳር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሲሳይ÷ ትንባሆና የአልኮል ውጤቶችን አብዝቶ መጠቀም፣ የሰውነት ክብደት መጠን መጨመርና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚመዘገበው የሟቾች ቁጥር በስኳር፣ ደም ግፊትና መሰል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ43 ነጥብ 3 በመቶ በላይ ሆኗል።
በተለይ የስኳር ህመምን በወቅቱ አለመታከም ለሌሎች በሽታዎች የሚያጋልጥ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሲሳይ፣ በተደረጉ ጥናቶች ጤናማ ያልሆነ የስኳር መጠን በአዋቂዎች ብቻ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
የትምባሆ እና የአልኮል ውጤቶችን አለመጠቀም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር፣ እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ ምግቦችን መመገብ በማዘውተር ጤናማ መሆን ይቻላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.