Fana: At a Speed of Life!

በወ/ሮ ዳግማዊት የተመራ ልዑክ በመንገድ ደህንነት ላይ ባተኮረው 3ኛው ዓለም አቀፍ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተካፈለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ትኩረቱን በመንገድ ደህንነት ላይ ባደረገው 3ኛው ዓለም አቀፍ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተካፈለ።

3ኛው ዓለም አቀፍ የሚኒስትሮች ስብሰባ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ለሶስት ቀናት ተካሂዷል።

“የ2030 ዓለም አቀፍ ግቦችን ማሳካት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከ140 ሃገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 700 ተሳታፊዎች፣ ከ80 በላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም በርካታ የግሉ ዘርፍ፣ ህዝባዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክም በቆይታው በርካታ የፓናል ውይይት መድረኮች ላይ መሳተፉን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አስታውቀዋል።

ከስብሰባው ጎን ለጎንም የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ከስዊዲኑ የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ቶማስ ኢነሮዝን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት ሚኒስትሮችና የስራ ሃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በውይይታቸውም ሃገራቱ የመንገድ ደህንነትን በማስጠበቅ ዙሪያ ያላቸውን ልምድ ለማካፈል በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

መድረኩ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በዘርፉ እያከናወነ ላለው ስራ አስፈላጊ ግብዓቶችን ያገኘበት መሆኑን በመጥቀስ፥ በቀጣይ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.