Fana: At a Speed of Life!

በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በጎርፍና ውኃ መጥለቅለቅ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 22 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚንስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በጎርፍና ውኃ መጥለቅለቅ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 22 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
የጣና ሐይቅ ሞልቶ በመፍሰሱ ምክንያት በደቡብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለጣና አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች የውኃ መጥለቅለቅ ተከስቶ በሰብልና በመኖሪያት ላይ ጉዳት ማድረሱን የሚታወቅ ነው።
የርብና ጉማ ወንዞችም ከመጠን በላይ በመሙላት በጎርፍ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስትርና ጉምሩክ ኮሚሽን በቅንጅት 22 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚገመት ስኳር፣ የምግብ ዘይትና አልባሳት ለአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አስረክበዋል።
በርክክቡ ላይ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ‘‘ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የፌዴራል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል’’ ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው ዘላቂ መፍትሔ እስከመስጠት መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ ገልፀው፤ ለተደረገው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።
በጊዜያዊነት ከመደገፍ ጀምሮ የአካባቢውን የጎርፍ አደጋ ስጋት በዘላቂነት ለመፍታት ከእርሻ ቦታቸው ሳይርቁ ሌላ ቦታ የሚሰፍሩበትን አማራጭ የክልሉ መንግሥት እያጤነ መሆኑንም ርእሰ መሥተዳድሩ መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።
በተለይ የርብ ግድብ በቀጣይ ዓመት ለጎርፍ አደጋ መንስኤ ከመሆን ወጥቶ ለመስኖ ልማት እንዲውል ‘‘ማጠናቀቁ ላይ በማተኮር ይሠራል’’ ነው ያሉት ርእሰ መሥተድሩ።
የማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች አስተዳዳሪዎች ለተደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.