Fana: At a Speed of Life!

በድምፃችሁ ውሳኔያችሁን ማሳወቃችሁ የስልጡንነት መገለጫና የትክክለኛ ዲሞክራሲ ማሳያ ነው – የፌዴሬሽን ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድምፃችሁ ውሳኔያችሁን ማሳወቃችሁ የስልጡንነት መገለጫና የትክክለኛ ዲሞክራሲ ማሳያ ነው ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ፡፡

ምክር ቤቱ የክልሉን በይፋ መመስረት ተከትሎ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም ፡-

በውበቷ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትኖሩ የተከበራችሁ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣የሸካ ሕዝቦችና የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የዲሞክራሲ ልምምዳችንን ደረጃ ከፍ የሚያደረግ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በህገ መንግሥቱ መሠረት በማድረግ 11ኛው የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ሆናችሁ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመንግስት ምስረታ ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ።

የፌደራል ስርዓታችን ልዩ ባህሪ የሆነውን ራስን በራስ የማስተዳዳር ህገ መንግስታዊ መብት መጠየቅ እንደ ስህተት የሚቆጥር ስርዓትና የውሸት ፌዴራሊዝም፣ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ላይመለስ አስወግዳችሁ፣ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ እንዲሁም ትክክለኛ የፌደራል ስርዐት እንዲኖር መሠረት ስለጣላችሁ፣ የረጅም ጊዜ ጥያቄያችሁ መልስ ስለአገኘ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ።

እንዲሁም መተዳደር የምትፈልጉበትን የአስተዳደር ክልል በድምፃችሁ ውሳኔአችሁን ማሳወቃችሁ የስልጡንነት መገለጫና የትክክለኛ ዲሞክራሲ ማሳያ ሲሆን የይስሙላው ፌዴራሊዝም ማብቂያ መሳያ ነው።

የተከበራችሁ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎችና መላ የሀገራችን ህዝቦች፣ ዛሬም በዉጭ ሃይል ተነድቶ የራሳቸውን ከፋፋይ ፍላጎት በህዝባችን ላይ ለመጫንና ካልተሳካ ደግሞ ሀገር ለማፍረስ የሚሯሯጠው የህወሓት አሸባሪ ቡድንና ተላላኪዎቹን በተባበረ ክንድ ቀብረናቸው የአድዋን ታሪክ ልንደግም ይገባናል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ሎአለዊነታቸውን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን በጋለ ስሜት እየገለፁ ባሉበት ወቅት የውጭ ጣልቃ ገብነት ፍላጎት፣ የዓለም ዲፕሎማሲን ጥላሸት መቀባት መፈለግ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል።

በተለይም በአንዳንድ ሀገሮች ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን በመዘንጋት፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰጡት አስተያየትና የውሸት ዘገባ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ÷ የኢትዮጵያ ህዝብ ሉዓላዊነቱንና የአገሩን ክብር አሳልፎ እንደማይሰጥ በዓለም አደባባይ ጭምር አስመስክሯል፣ እያስመሰከረም ይገኛል።

በዚህ ረገድ በውስጥና በውጭ አገራት የምትኖሩ ውድ ኢትዮጵያውያን ክብርና ምስጋና ይገባቸኋል።

አሁንም የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ፈለግ በመከተል ሀገራችንን ለማዳን የምንዘምትበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

በመጨረሻም አሁን አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም ዜጋ አካባቢውን ከወራሪዎችና ከአፍራሽ ኃይሎች ተግቶ በመጠበቅ የአገሪቱን ህልውናና የሕዝቦችን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ አጽእኖት የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ሲሆን ÷ ከዚሁ ጎን ለጎን በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ ለጥምር ጦርና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አሰፈላጊ መሆኑን እየገለፅን ÷ አዲሱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብና መንግስት መጭው ጊዜ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆን እየተመኘን የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድጋፍ አይለያችሁም፡፡

“ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት”!

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.