Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዘነበ ከበደ ከስዊዘርላንድ የፓርላማ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ከስዊዘርላንድ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፍራንዝ ግሩተር እና ከስዊዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ አምባሳደር ሲሪ ዋልት ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ዘነበ በውይይታቸው ላይ÷ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ የኢትዮጵያ መንግስት ያከናወናቸውን ተግባራት፣ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እንዲሁም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡
የስዊዘርላንድ መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በህወሓት ወረራ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታም መክረዋል፡፡
የስዊዘርላንድ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፍራንዝ ግሩተር በበኩላቸው÷ በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮችን ይዘው ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩና ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ከስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ሲሪ ዋልት ጋር ተወያይተዋል፡፡
የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር በቀጣዩ መስከረም ወር መጀመሪያ በአዲስ አበባ የፖለቲካ ምክክር ለማካሄድ ታሰቦ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሲሪ ዋልት ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.