Fana: At a Speed of Life!

ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን ይገባል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ህዝበ ክርስቲያኑ አብሮነቱንና አንድነቱን በማጠናከር እርስ በርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት በዓለ ትንሳኤውን ሊያከበር ይገባል ብለዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በፆም ወቅት ያሳየውን መልካም ተግባራትን በበዓሉም ወቅት በማጎልበት የተራቡትን በማብላት እንዲሁም የተጠሙትን በማጠጣትና ህሙማንን በመጠየቅ ወገናዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የክርስትና አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት መልካም ነገሮችን በመፈጸም ለቆዩና በነገው እለት የትንሳኤ በዓልን ለሚያከብሩ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር በመደጋገፍና በመረዳዳት የቆየ ባህላችንን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በተለይ አቅመ ደካማ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልሉ ሕዝብ በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴቶች እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ያለውን መቻቻልና መተባበር የበለጠ እንዲጠናከር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሚናውን መወጣት እንደሚኖርበት አስታውቀዋል።

በተለይም በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ህዝቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓለ ትንሳኤው ክርስቶስ የአዳም ዘርን ነፃ ያወጣበት ክብረ በዓል በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ የዘረኝነትና የጎሰኝነት አስተሳሰቦችን በማስወገድ በዓለ ትንሳኤውን በአንድነትና በመደጋገፍ እንዲያሳልፈው አሳስበዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ዘላቂ የሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ረገድ ምዕመኑ የበኩሉን እንዲያበረክት ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.