Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት መሆኑን እንደቀጠለበት መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት መሆኑን መንግስት ገለፀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፥ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ በስም ለመነገጃነት ከማዋል ውጪ ቆሜለታለሁ ብሎ ለሚሰብከው ህዝብ እንኳ ሰብዓዊነት የማይሰማው መሆኑን አመልክቷል።

ለአብነትም ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡት 1010 ተሽከርካሪዎች ተመልሰው ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ እንዲመለሱ በማድረግ ፋንታ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወራሪ ኃይል አማራና አፋር ክልልን ሲወር የሠራዊቱ ማጓጓዣ አድርጐ እንደተጠቀመባቸው ነው የገለፀው።

ይባስ ብሎ በጊዜያዊነት ወረራ አድርጐ ከቆየባቸው እንደ ኮምቦልቻና ሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ የመንግሥትና የግል መጋዘኖች የዘረፈውን ስንዴና ሌሎች ምግብና ምግብ – ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች በትግራይ ክልል በሚገኙ መጋዘኖች ካከማቸ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ማስገቢያ በሆነው በአብዓላ መስመር ወረራ በማካሄድና የከባድ መሣሪያ ተኩስ በመክፈት መስመሩ እንዲዘጋ ማድረጉን አመልክቷል።

እንደ አለም ጤና ድርጅት አይነት ለሁሉም ሰው በእኩል ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ግን አሸባሪው ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ሀስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዙ አልተደመጡም ብሏል።

ይልቁንም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል የአሸባሪው ቡድን የሚያሰማውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው እያስተጋቡት ይገኛሉ ያለው መግለጫው፥ ይህ በመንግስት ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኗል፣

የትግራይ ክልል ህዝብ ሰብዓዊ የምግብና ምግብ – ነክ ያልሆነ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲቀርብለት፣ የክልሉ አርሶ አደር የክረምት ዝናብን በመጠቀም የራሱን ምርት እንዲያመርትና ከዕርዳታ እንዲላቀቅ መንግስት ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ይህን በጐ ዓላማ ያነገበውን የመንግሥት የተናጠል ውሳኔ ወደ ጐን በማድረግ የፀረ – ህዝብና የሽብር አቋሙን በግልፅ ያሳየበትን ተግባር የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር እንዲሁም በክልሎቹ በሚገኙ ንጹሃን ላይ እጅጀግ ዘግናኝ ወንጀሎችን በመፈጸም ለእኩይ አላማ የቆመ ቡድን መሆኑን በግልፅ አስመስክሯል፡፡
መንግሥት ለትግራይ ህዝብ ባለው ውግንናና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጐል በአፋር ክልል በአብአላ በኩል በቀጥታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዝ ባስቀመጠው አቅጣጫ እንዲሁም የአፋር ክልል መንግሥትና ህዝብ ለትግራይ ክልል ባላቸው አጋርነት እ.ኤ.አ ከጁላይ 12/2021 ዓ/ም ጀምሮ በ1010 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ በስም ለመነገጃነት ከማዋል ውጪ ቆሜለታለሁ ብሎ ለሚሰብከው ህዝብ እንኳ ሰብዓዊነት የማይሰማው በመሆኑ ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡት 1010 ተሽከርካሪዎች ተመልሰው ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ እንዲመለሱ በማድረግ ፋንታ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወራሪ ኃይል አማራና አፋር ክልልን ሲወር የሠራዊቱ ማጓጓዣ አድርጐ ተጠቅሞባቸዋል፡፡

ይባስ ብሎ በጊዜያዊነት ወረራ አድርጐ ከቆየባቸው እንደ ኮምቦልቻና ሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ የመንግሥትና የግል መጋዘኖች የዘረፈውን ስንዴና ሌሎች ምግብና ምግብ – ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች በትግራይ ክልል በሚገኙ መጋዘኖች ካከማቸ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ማስገቢያ በሆነው በአብዓላ መስመር ወረራ በማካሄድና የከባድ መሣሪያ ተኩስ በመክፈት መስመሩ እንዲዘጋ በማድረግ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 15/2021 ጀምሮ ዕርዳታ እንዳይቀርብ አስተጓጉሏል፡፡

እንደ አለም ጤና ድርጅት አይነት ለሁሉም ሰው በእኩል ቆመናል የሚሉ አለምአቀፍ ተቋማት ግን አሸባሪው ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ሀስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዙ አልተደመጡም።

ይልቁንም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል የአሸባሪው ቡድን የሚያሰማውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው እያስተጋቡት ይገኛል። ይህ በመንግስት ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም።

አሁንም ለአንድ ወገን ባጋደለው አቋማቸው በመጽናት የሽብር ቡድኑ ወደ ትግራይ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት መሆኑን በግልጽ አለማንሳታቸው በተዛባ አመለካከታቸው መጽናታቸውንና ውግንናቸው ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለፖለቲካ አጀንዳ መሆኑን ያመለክታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ክልል ህዝብ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲቀርብ ለማስቻል በየጊዜው ከአጋር አካላት ጋር ምክክር በማድረግ እየሠራ ይገኛል።

ምንም እንኳ ቀደም ብለው ዕርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ገብተው ያልተመለሱ 1010 ከባድ ተሽከርካሪዎች በክልሉ መኖራቸውን እያወቀ በዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለቤትነት ሥር ያሉ 118 ከባድ ተሽከርካሪዎች በሙሉ አቅማቸው የዕርዳታ ማጓጓዝ ሥራ እንዲሰሩ ፈቅዷል፡፡ ዕርዳታውን ለሚያጓጉዙ ሾፌሮችም ሙሉ የደህንነት ዋስትና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ከዚህም በላይ በቀጣይነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የዕርዳታ አቅርቦቱ ያለ እንቅፋት እንዲከናወን ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ነው፡፡

በመጨረሻም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና አጋር አካላት የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን እኩይ ተግባርና የእርዳታ እንቅስቃሴ አደናቃፊነት እንዲኮንኑ እያሳሰብን መንግሥት እንደ ወትሮው የዕርዳታ አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የበኩሉን ሁሉ እንደሚወጣ እንገልጻለን፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.