Fana: At a Speed of Life!

ወቅታዊውን መሰናክል ለመሻገር በህብረት መቆም እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ህብረታችንና አንድነታችን ከጠነከረ የማንሻገረው መሰናክል፤ የማናልፈው ችግር የማንቋቋመው ጫና አይኖርም” ሲሉ ለረጅም ዓመታት በውጭ አገራት የኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ።
ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ አገራት በየዘመኑ የተለያዩ ተስፋና ፈተናዎች ውስጥ ያልፋሉ።
በተለይም ደግሞ ደሃ አገራት ከተስፋ ይልቅ ጫና ውስጥ የሚገቡበት ክስተት በስፋት የተስተዋለ ታሪክ ነው።
እነዚሁ አገራት በአንድነትና በሕብረት የቆሙት ፈተናውን ሲሻገሩ የተከፋፈሉት ግን ወደ ማይወጡት አዘቅት ውስጥ ገብተዋል ይላሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ዳያስፖራዎች።
አቶ ኤልያስ ወንድሙ ለ24 ዓመታት በአሜሪካ አገር የኖሩና የጸሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት የውጭ ተጽዕኖ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ምዕራባውያን የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ለዘመናት የተጠቀሙበት ስልት ነው።
”እነሱ የሚፈልጉት የራሳቸውን ሕዝብ ማስፋት፣ ለትውልድ የሚተርፋቸውን የእርሻ መሬት መያዝ እና በዚያም ላይ የሚሰራ የሰው ኃይል ማግኘት ነው” ብለዋል።
”ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ የተነሱት ለዚሁ ነው” የሚሉት አቶ ኤልያስ ”ኢትዮጵያዊያን ለዚያ የሚሆን ስብዕና የለንም፤ እንደ አገርም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትቆም ናት” ይላሉ።
እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ አሜሪካም በአፍሪካ ቀንድ ላይ አዲስ የፖሊሲ ለውጥ አድርጋለች፤ ይኸው የፖሊሲ ለውጥ ተግባራዊ እንዲሆንላትም የተለያዩ ስራዎችን ጀምራለች።
ይህን ጫና ለመመከት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ በአንድነትና በሕብረት መቆም አለባቸው ብለዋል።
”ህብረታችንና አንድነታችን ከጠነከረ የማንሻገረው መሰናክል፤ የማናልፈው ችግር የማንቋቋመው ጫና አይኖርም” ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያዊያን የግል ጥቅምና ፍላጎታቸውን ገታ አድርገው ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፉ ጠይቀዋል።
ላለፉት 43 ዓመታት በተለያዩ የምዕራብ አገራት በሕክምና ሙያ ያገለገሉት ዶክተር ሰለሞን ማሞ “ምዕራባውያን ጫና ከመፍጠር አይቆጠቡም” ይላሉ።
”የአሁኑ ትንሽ ከበድ አለ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ጊዜም በፈተና ውስጥ ያለፈ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የምዕራባውያንን ፍላጎት ለማሟላት የተንበረከከበት ጊዜ የለም ሲሉም ይናገራሉ።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጀመረውን የአንድነትና የትብብር መንገድ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
አገር ከምንም በላይ መሆኑ ታውቆ ለዚህ በአንድነትና በመተባበር የአገር ሉዓላዊነትን ማስቀጠል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪው ሕወሓት ጋር እያደረገ ያለውን ጦርነት ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙኃኑ ትክክለኛውን ገጽታ እያንጸባረቁ አለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.