Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልል መንግስት በክልሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
 
የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ የክልሉ መንግስት አዋጁ በተሻሻለው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህግ መንግስት አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ 8 እንዲሁም አንቀፅ 103 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት መውጣቱን አስታውቀዋል።
 
በዚህም የክልሉ መንግስት ካቢኔ ስራ አስፈፃሚ በትናንትናው እለት ምሽት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልፀዋል።
 
ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫም ዝርዝር ውሳኔውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት፤
 
• በትግራይ ክልል ከገጠር ወደ ከተማ፤ ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከከተማ ወደ ከተማ የሚደረጉ ዝውውሮች ተከልክለዋል።
 
• ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው የገበያ ማዕከላት፤ ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚከናወንባቸው እንደ ሰርግ፣ ተስካር እና መሰል ክንውኖች እንዲሁም በክልሉ የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተከልክለዋል።
 
• የንግድ ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጫት ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛ ክለቦች እና ሌሎችን ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል።
 
• በክልሉ የሚካሄዱ ማናቸውም ስብሰባዎች መታገዳቸውንም ገልፀዋል
 
• የመንግስት ሰራተኞችን በተመለከተም ነብሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ እድሜያቸው ለጡረታ የተቃረቡ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑንም አስታውቅዋል።
 
• መንግስታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎችና ጽህፈት ቤቶችን በተመለከተ በሚያወጡ መርሃ ግብሮች ስራቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል ብለዋል።
 
ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በመግለጫቸው በማከልም ውሳኔው በትግራይ ክልል ደረጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተቋቋመ ግብረ ኃይል ያጠናው 22 ጉዳዮችን የያዘ ጥናት ላይ መሰረት ተደርጎ የተወሰነ መሆኑንም ገልፀዋል።
 
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተላለፈው ውሳኔዎች ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.