Fana: At a Speed of Life!

የአዲሱ መንግስት ምስረታ ሂደት ለዴሞክራሲ መጎልበት ተስፋ የሚሰጥ ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲሱ መንግስት ምስረታ ሂደት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መጎልበት ተስፋ የሚሰጥ መልካም ጅምር ከመሆን ባለፈ የአዲስ ምዕራፍ ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ሰለሞን ጎራው እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የተካሄዱ አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች የይስሙላና የውሸት ነበሩ።
ከምርጫው በፊትና በኋላ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት፣ ምሁራንና ንጹሃን ዜጎች ለሞትና ለእስራት የሚዳረጉበት ሁኔታም እንደነበር አስታውሰዋል።
የህዝብ ድምጽ በማጭበርበር ሲመሰረት የነበረው መንግስት የባለስልጣኖችን ኪስና ካዝና ከመሙላትና ህዝቡን ወደ ቀውስና ችግር ከማስገባት ውጭ ለውጥም ሆነ እድገት አላመጣም ብለዋል።
ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተሻለ መልኩ ሰላማዊ ከመሆኑም ባለፈ ህዝቡ ይመራኛል፣ ያስተዳድረኛል ያለውን ፓርቲ በነጻነት የመረጠበት በመሆኑ የዴሞክራሲ መልካም ጅምር ሆኖ መመዝገቡን ተናግረዋል።
በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ በሰላማዊ ሂደት መንግስት መመስረቱን ጠቁመው÷ ይህም ለቀጣይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መጎልበት መልካም ጅምርና ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የምስረታ ሂደቱ በዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ የአዲስ ምዕራፍ ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።
አቶ ሰለሞን እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ዘመኑ ያበላሻቸውን በርካታ ጉዳዮች አዲሱ መንግስት የማስተካከል ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
በተለይ ግለጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሰራር እንዲሁም ሌብነት በአገሪቱ ስር መስደዱን ጠቁመው÷ በፍጥነት ካልተስተካከለ ወደባሰ ቀውስና ድህነት እንደሚያስገባ ተናግረዋል።
ባለስልጣንን ጨምሮ በሌብነት ተግባር የሚሰማራ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት ትክከለኛ አሰራር ለመዘርጋት መመሪያና ደንቦችን ዳግም መፈተሽ እንደሚገባም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሰላም፣ የዴሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ በበኩላቸው÷ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩና ዴሞክራሲ ናፋቂ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የውሸት ዴሞክራሲ ተለውጦ አሁን መልካም ጅምር መታየቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ያሉት ዶክተር አልዩ÷ ህዝቡም ጅምሩ ውጤታማ እንዲሆን መደገፍ አለበት ብለዋል።
ዶክተር አልዩ አንዳሉት ከምርጫው እስከ መንግስት ምስረታው የነበረው ሂደት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሂደት እንዲጎለበት ከማድረግ ባለፈ አዲስ ምዕራፍ ያሳየ ነው።
በህዝብ ይሁንታ የተመሰረተው አዲሱ መንግስት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ የማሳደግ አቅምና ብቃት አለው የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
አዲሱ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የህግ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ ያለእረፍት መስራት ይኖርበታል፤ ግልጽነትና ተጠያቂነትም ማስፈን አለበት ብለዋል፡፡
በሰላምና ልማት እጦት የተሰቃየው ህዝብ ከመንግስት ብዙ ይጠብቃል፤ በመሆኑም መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር ማሳየት ይኖርበታል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህርት ወይንሸት ውቤ ናቸው።
እንደ መመህርቷ ገለጻ ÷ መንግስት የጀመረውን ተስፋ ሰጭ የዴሞክራሲ ጉዞ አጠናክሮ የውጭ ዲፕሎማሲውን ማሻሻልና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከህዝብ ጋር ማስጠበቅ ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና አገር ለማፍረስ የሚያደርገውን መፍጨርጨር ለማስቆም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ እንዳለበትም ነው የገለጹት።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.