Fana: At a Speed of Life!

የካፒታል ገበያ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የካፒታል ገበያ ኩባንያዎችና ገዥዎች የሚገናኙበትን ፍትሃዊና ቀልጣፋ የግብይት ስርዓት የሚፈጥር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ መለስ ምናለ፤ የረቂቅ አዋጁን ዋና ዋና ነጥቦችና አስፈላጊነቱ ላይ ለውይይቱ ታዳሚዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የካፒታል ገበያ የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ቆጣቢዎችንና የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ፈላጊዎችን የሚያገናኝ የገበያ አይነት መሆኑን አንስተዋል።

ረቂቅ አዋጁ በተለይ በአክሲዮን ገበያ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሃብቶች መብትና ጥቅምን የሚያስከብር መሆኑንም ገልጸዋል።

”ሰነደ መዋዕለ ነዋይ” የሚባሉ የተለያዩ ገንዘብ አዘል የሆኑና በገበያ ላይ ሊሸጡ የሚችሉ ሰነዶች፣ ሰነዱን የሚሸጡ ኩባንያዎችና ገዥዎች የሚገናኙበትን ፍትሃዊና ቀልጣፋ የመገበያያ ስርዓት ይፈጥራልም ብለዋል።

በተጨማሪም በፋይናንስ ዘርፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መዋቅራዊ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ታስቦ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እንደ አቶ መለስ ገለፃ አሁን ባለው የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ኢኮኖሚው የተመረኮዘው በባንክ በሚቀርብ ፋይናንስ ላይ ብቻ ነው።

ባንኮችም የአጭር ጊዜ ቁጠባን ሰብስበው ለአጭር ጊዜ የማበደር እንጂ ለረዥም ጊዜ የማደበር ስራን የማይሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ይህም የረዥም ጊዜ ቆጣቢዎች እንደ ማህበራዊ ዋስትና፣ መድህን ድርጅቶችና ግለሰቦች ለረዥም ጊዜ ቆጥበው ፋይናንሳቸውን ኢንቨስት ማድረግ ቢፈልጉ የካፒታል ገበያ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።

ስለሆነም የካፒታል ገበያ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ በእጅጉ አስፈላጊና ችግር ፈቺ መሆኑን ገልጸዋል።

የካፒታል ገበያ ማለት ገዢዎችና ሻጮች በፋይናንስ ደህንነት የንግድ ማእቀፍ ውስጥ የሚሰማሩበት እንደ ቦንድ፣ አክሲዮን እና የመሳሰሉትን ያካተተ ገበያ ነው።

የካፒታል ገበያ ትሩፋቶች ዛሬ ላይ በዓለም በተለይ በግሉ ዘርፍ ቁጥር አንድ የካፒታል ማሰባሰቢያ መንገድ በመሆን እያገለገለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.