Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ አካላት እስከ 3 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣሉ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከፊታችን ሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ 19 ወረርሽን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በሚጥሱ ሰዎች እና ተቋማት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ።

የጤና ሚኒስቴር እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋዜጣዊ መግለጫ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሰዎች እንቅስቃሴና ማህበራዊ ተግባራት ላይ ክልከላ የሚጥልና በወንጀል የሚያስጠይቅ መመሪያ ይፋ አድርገዋል።

መመሪያውን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይም እስከ 3 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች እንደሚያስቀጣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

በመመሪያው መሰረት ማንኛውም የኮሮና ቫይረስ ያለበት ግለሰብ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ ተከልክሏል::

ቫይረሱ የተገኘበት ሰውም ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፣ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚያስችል ሁኔታም ንክኪ ማድረግ በህግ የሚያስቀጣ ሆኗል::

በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርግ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ÷የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ያላደረገ ሰውን እንዳያስተናግዱ መመሪያው ያዛል::

የትራንስፖርት የስፖርትና ሌሎች ማህበራዊ መሰባሰቦችን በሚመለከትም ተቋማቱ በሚያወጧቸው ዝርዝር ደንቦች የሚፈፀሙ ይሆናል::

ስብሰባን በሚመለከትም ማንኛውም ሰብሳቢ አካል ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባራትን በመከወን የተሰብሳቢዎችን ቁጥር 50 ብቻ እንዲሆን ተወስኗል::

አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ለሰላም ሚኒስቴርና ለጤና ሚኒስቴር እንዲያሳውቅ መመሪያው አስቀምጧል::

መመሪያውም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ማስታወቁን ከአዲስ ሚድያ ኔትወርክና ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.