Fana: At a Speed of Life!

የዲቼቶ እና ጋድ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሥምምነት ተቋረጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲቼቶ እና ጋድ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሥምምነት እንዲቋረጥ መደረጉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ቢሮ የመንግሥትና የግል አጋርነት እና የግል የኤሌክትሪክ ኃይል አልሚዎች ፕሮጀክት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጥላዬ እንደገለፁት÷ ሥምምነቱ የተቋረጠው አክዋ ፓወር የተሰኘው የሳዑዲ አረቢያ ኩባንያ ፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡
የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትም÷ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ እና ብሔራዊ ባንክ በጋራ ውይይት በማድረግ በቀጣይ በግል አልሚዎች ለሚገነቡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዋስትና እንዲሰጣቸው መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው ለአራት የተለያየ ጊዜ የማራዘሚያ ጥያቄ አቅርቦ የተፈቀደለት ቢሆንም÷ የገንዘብ አቅርቦቱን ማሳካት እንዳልቻለ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ሳቢያ ውሉን እንዳቋረጠ ቢገልፅም÷ ዋናው ምክንያት ግን የውጭ ምንዛሬ ቅያሪ ዋስትና መንግሥት እንዲሰጠው መፈለጉ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
የኃይል ግዥ ሥምምነቱ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ላይ መፈረሙን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ÷ ኩባንያው ፕሮጀክቶቹ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጠው እንዲቆዩለት መጠየቁና በሌሎች የመደራደሪያ ነጥቦች መግባባት ላይ መድረስ ባለመቻሉ በመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ ውሳኔ መሠረት ኮንትራቱ በሁለቱ ወገኖች ሥምምነት እንዲቋረጥ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው አንድ ኪሎ ዋት በ2 ነጥብ 526 የአሜሪካን ሳንቲም የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም÷ በጊዜ ገደብ ብርን ወደ ዶላር የመቀየር ዋስትና በኮንትራቱ ውስጥ እንዲካተትለት መጠየቁ ለውሉ መቋረጥ መንስኤ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
ኩባንያው እስከ 75 በመቶ የፕሮጀክቱን ፋይናንስ ከአበዳሪ ተቋማት እንዲሁም እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ከግል አልሚው፣ ከባለአክሲዮኖች እና ከስፖንሰሮች በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ሊያቀርብ ተስማምቶ ነበር፡፡
የዲቼቶ እና ጋድ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን÷ ኩባንያው የዲቼቶን በ18 እንዲሁም የጋድን በ15 ወራት ግንባታቸውን አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ አቅዶ እንደነበር መናገራቸውን ከኤሌክትሪክ ኃል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.