Fana: At a Speed of Life!

“ያለማስክ መንቀሳቀስ ጠጥቶ እንደማሽከርከር ነው” የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በወቅታዊ የኮቪድ 19 ሁኔታ ዙሪያ የጤና ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት÷ እስካሁን ባልታየ መልኩ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተያዙ ነው ብለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በበሽታው ተይዘው በጸና የታመሙ ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መሆኑን እና ከተመረመሩ መቶ ሰዎች መሃከል በአማካይ እስከ 23 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ገልጸዋል

ከዚያም ባለፈ በኮቪድ 19 ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

ህሙማን  በጤና ተቋም ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን  ኦክስጅን እቤታቸው ውስጥ መውሰድ በመጀመራቸው የተነሳ ማግኘት የሚገባቸውን የተሟላ  ህክምና በወቅቱ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን አንስተዋል።

ዶክተር ሊያ  አያይዘውም ተመርምረው ቫይረሱ እንዳለባቸው እያወቁ ራሳቸውን የማያገሉ በርካታ ሰዎች ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው÷ ወረርሽኙ እየጨመረ ቢሆንም ጥንቃቄ እየቀነሰ በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሰው ህይወት ሊጠፋ ስለሚችል የፀጥታ አካላት በስራ ላይ ባለው መመሪያ መሰረት ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በተለይም መሰባሰቦች በሚታዩባቸው በትራንስፖርት፣ በገበያና በቤተእምነቶች  አካባቢ ርቀትን መጠበቅ፣ማስክ ማድረግና አለመነካካት በዋናነት ያለምንም ግፊት ህብረተሰቡ ሊተገብረው የሚገባ ቢሆንም ፖሊስ ተገቢውን እገዛና ክትትል ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ቀናትም አስፈላጊ የሆኑ የህግ ማስፈጸሚያ ስልቶች ግልጽ ተደርጎ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ አካላት ይተላለፋል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.