Fana: At a Speed of Life!

ጸጥታ ሃይሉና ህዝቡ ተቀናጅቶ በመስራቱ በመዲናዋ ላይ የታቀደው የጥፋት ሴራ ከሽፏል – ዶ/ር ቀነአ ያደታ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጸጥታ ሃይሉ እና የከተማው ህዝቡ ተቀናጅተው በጋራ በመስራታቸው አዲስ አበባ ላይ የታቀደው የጥፋት ሴራ መክሸፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ ገለጹ፡፡
 
ዶክተር ቀነአ በፋና ቴሌቪዥን “ስለ ኢትዮጵያ” ዝግጅት ላይ እንደተናገሩት፥ በመዲናዋ የጥፋት ሃይሎች ሊጠቀሙበት የነበረ የጦር መሳሪያዎች በጸጥታ ሃይሎችና በህዝቡ ቅንጅት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም ቦምቦች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ በግለሰብ ደረጃ የማይፈቀዱ የመገናኛ ሬዲዮዎች፣ በርካታ ወታደራዊ አልባሳት፣ ገንዘቦች፣ የኢትዮጵያ እና የሌሎች አገራት ሲም ካርዶች እና ሌሎች መሰል ቁሳቁሶች ተይዘዋል ነው ያሉት፡፡
 
በዚህም የመዲናዋን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ በሽብር ቡድኖቹ ታቅዶ የነበረውን የሽብር ሴራ ማክሸፍ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
 
ከዚህ በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ምዝገባም በተሳካ መልኩ በመከናወኑ በርካታ የጦር መሳሪያዎች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡
 
ሰላማዊ ዜጎችን እና የጥፋት ሃይሎችን ለመለየትም ጊዜያዊ መታወቂያ በጥንቃቄ ተሰጥቷል ያሉት ሃላፊው፥ ከተመዘገቡት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ 43 በመቶው ህገወጥ እና ለሽብር አላማ ሊውሉ የነበሩ መሆናቸውን ሃላፊዉ ገልጸዋል፡፡
 
ከህዝቡ እና ከጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት በተጨማሪ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ የጸጥታ ተቋማት ተናበው መስራታቸው በጥፋት ሃይሎች የታቀደው የሽብር ሴራ ሊከሽፍ እና ከተማዋ ሰላሟን ጠብቃ እንድትቀጥል ማድረግ መቻሉንም ዶክተር ቀነአ አውስተዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ነዋሪ 24 ስዓት ቀንም ሌሊትም ሮንድ ሆኖ አካባቢውን በመጠበቅ እያደረገ ያለው ተሳትፎ እጅግ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
ነዋሪዎች ምንም አይነት ኮሽታ ሲኖር ለጸጥታ ሃይሉ መረጃ በመስጠት እና ከዚያም አልፎ ለጸጥታ አካላቱ ምግብ እና መጠጥ በማቅረብ መልካም ስራዎች ሰርተዋል፤ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡
 
የከተማ አስተዳደሩ ግንባር ድረስ በመሄድ ሰራዊቱን በሁለንተናዊ መንገድ በመደገፍ እየተወጣ ያለው ሚና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
 
በአመለወርቅ ደምሰው
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
 
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
 
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
 
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.