Fana: At a Speed of Life!

ፋኦ በኢትዮጵያ ለአንበጣ መከላከያ የ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የ4 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ እና የኬሚካል ርጭት በመጠቀም ስርጭቱን 90 በመቶ መቀነስ ተችሏል።

ይሁን እንጅ በአንዳንድ ቦታዎች በባህላዊ መንገድ ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የአንበጣ መንጋው ስለሚበታተን የቁጥጥር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።
የአንበጣ መንጋው ከመካከለኛው ምስራቅ በመነሳት በየመንና ሶማሊያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፥ ሶማሌ፣ አፋር፣ ምስራቅ አማራና ደቡብ ትግራይ አካባቢዎችን እንደሚያዳርስም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የንፋሱ አቅጣጫ በመቀየሩ ከሳዑዲ ዓረቢያና ፓኪስታን በመነሳት በደቡባዊ ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በመዛመት ወደ ኬንያ ይሻገራልም ነው ያሉት።

የአንበጣ መንጋው ከተበተነ በኋላ የት እንደተሰበሰብ ለማወቅ፥ በድሮን የታገዘ የመረጃ አሰባሰብ ስልት ለመጠቀም ከቻይና መንግስት ድጋፍ ለማግኘት እየተነጋገሩ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

የበረሃ አንበጣው በምስራቅ አፍሪካ እስከ መጭው ነሐሴ ወር ሊቆይ እንደሚችል ትንበያ መኖሩን ጠቅሰው፥ ይህን ታሳቢ በማድረግም በባህላዊ መንገድና በአውሮፕላን ርጭት ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን አውስተዋል።

ለዚህ እንዲረዳም 30 ሚሊየን ብር መመደቡን አስረድተዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.