Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ወቅቱን ጠብቀው እየተሰራጩ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ለግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር የግብርና ግብዓት እና ወቅቱን የጠበቀ ስርጭት ማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ ገልፀዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በ2013/14 ምርት ዘመን 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የሚደርስ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከክልሎች መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደርም የ24 በመቶ ጭማሪ ወይም የ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ልዩነት ማሳየቱን አንስተዋል፡፡

ይህም የአርሶ አደሮች የግብዓት አጠቃቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የሣያል ያሉት ዳይሬክተሩ÷ በተያዘው ምርት ዘመንም አስካሁን ድረስ 85 በመቶ የሚሆነው ከጅቡቲ ወደብ ደርሶ ወደ ክልሎች እና በእያንዳንዱ ክልል ለአርሶአደሮች ለሚያሰራጩ የህብርት ስራ ማህበራት በመሰራጨት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ እንደማንኛውም ግዥ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ የዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታን በወቅቱ ማውጣትን የሚፈልግ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገራት በአለም ገበያ ተወዳድረን የምንገዘው በመሆኑ እና ከትራንሰፖረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ በመሆኑ መንግስት በሚኒስትር መስሪያቤቱ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተሳበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት ያህል በዓለም ገበያ የማዳበሪያ ዋጋ ሲጨምር መንግስት ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ለዘርፉ ድጋፍ በማድረግ የዋጋ ጭማሪው ከአርሶ አደሮቻችን አቅም በላይ እንዳይሆን ከፍተኛ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርስ በሊትር እና በኪሎ ግራም የሚለኩ የኬሚካል አቅርቦት እንዲሁም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሀገሪቱ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 43 በመቶ የሚሆነው አሲዳማ እና ከዚህ ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው ደግሞ አሲዳማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በኖራ በማከም እና ጤነኛ በማድረግ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.