Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ 11 ትምህርት ቤቶች እውቅና ተሰረዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ የሚገኙ ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ 11 ትምህርት ቤቶች እውቅና ተሰርዟል፡፡

የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ከደረጃ በታች ናቸው ያላቸውን የ11 ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፍቃድ መሰረዙን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ የትምህርት ተቋማት የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ ሂደትን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በመዲናዋ የሚገኙ የመንግስትም ሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ተገቢውን አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ በየሁለት ዓመቱ ምዘና እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

በመሆኑም የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የትምህርት ተቋማትን ከጥራት አንጻር የመለካት፣ ቁጥጥር የማድረግና በተቀመጠው ደረጃ መሰረት የመመዘን ስራዎች ተከናውነዋል።

እነዚህ 11 ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሂደትም ሆነ በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የጤናና የደህንነት ስጋት የሚያሰከትሉ መሆናቸው ስለተረጋገጠ የእውቅና ፍቃዳቸው መሰረዙን አስታውቀዋል።

ፍቃዳቸው ከተሰረዘው መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ለ ሱፐር ኪድስ፣ ኢንዱራንስ አዲስ፣ ኤልሻዳይ ወረዳ 12፣ ጵሾን ወረዳ 9፣ ቪካስ እና ሮሆቦት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሀሞና እና እመሙዝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ሁንዴ ጉዲና የመጀመሪያ ደረጃ እና ማይ ፊፍ ቅድመ መደበኛ እንዲሁም ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አዶናይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ 672 ነባር እና 51 አዲስ የቅድመ መደበኛ፣ የመደበኛ፣ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መመዘናቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል 723 ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው መለኪያ መሰረት 75 በመቶና ከዚያ በላይ በማምጣት የእውቅና ፍቃድና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

መለስተኛ ችግር ያለባቸውና በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራቸውን እያከናወኑ ለሚቀጥለው ዓመት ማሻሻያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው 61 ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ማሰጠንቀቂያው ከተሰጣቸው መካከል 29 የቅድመ መደበኛ፣ 28 የመጀመሪያ ደረጃና አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትምህርት ቤቶቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤያቸው እንዲሻር ለ2015 ዓ.ም የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ አቅርበው እንዲያስፈትሹ መመሪያ እንደተቀመጠላቸውም አብራርተዋል።

ባለፈው ዓመት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው 65 ትምህርት ቤቶች 60ዎቹ በተደረገ ክትትል የደረጃ ማሻሻል በማድረጋቸው የእውቅና ፈቃድ አግኝተዋል።

ምንም አይነት ማስተካከያና ማሻሻያ ያላደረጉ አምስት፣ ዘንድሮ በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መስፈርቱን ያላሟሉ ስድስት ትምህርት ቤቶች ተለይተዋል።

እውቅና ሳይኖራቸው ተማሪ የመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ከተገኙ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው÷ የተመዘገቡ ተማሪዎችን ሃላፊነት ባለስልጣኑ እንደሚወስድ አክለዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ያስመዘገቡበት ትምህርት ቤት እውቅና እንዳለው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

እውቅናቸው የተሰረዘ ትምህርት ቤቶች ዝርዝር በሚገኙበት ክፍለ ከተማ፣ ወረዳና ሕዝብ ሊያየው በሚችልባቸው አካባቢዎች እንደሚለጠፍም ነው ወይዘሮ ሸዊት የተናገሩት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.