Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 10 ወራት ከተኪ ምርቶች 418 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀት ዓመቱ ባለፍት 10 ወራት ከተኪ ምርቶች 498 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ለተኪ ምርቶች ትኩረት በመስጠት የሀገራችንን ብልጽግና እናፋጥናለን! በሚል መሪ ቃል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱንና ተጠሪ ተቋማቱን የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም እየገመገመ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከተኪ ምርቶች 498 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት የእቅዱን 84 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አፈፃፀሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ102 ሚሊየን ዶላር ወይም የ32 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡን አስረድተዋል።

ለዕቅድ ስኬቱ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ተቋማት መካከል ምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል፡፡

የአምራቾችን ችግሮች በውል ተረድቶ በመፍታትና የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የዘርፉን አገራዊ የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ ያለመ አገራዊ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነትነ በይፋ መጀመሩን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ንቅናቄው ከላይ እስከታች ባሉት የመንግስት መዋቅሮች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካሄዱን ገልፀው፥ ንቅናቄው የዘርፉን ችግር በመፍታት እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ፈተን የአገሪቱን የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት አቶ መላኩ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.