Fana: At a Speed of Life!

ነገ የሚጀምረው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያተኩራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ነገ መካሄድ የሚጀምረው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ በህግ የበላይነትና የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚመክር ተገለጸ።

የጨፌው አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ጨፌው ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ለጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደነበር በማስታወስ፥ ይህንንም ተከትሎ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊ ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።

ሆኖም አሁንም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ጨፌው ይሰራል ብለዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ባሉት ቋሚ ኮሚቴዎች ሲገመገም እንደነበር አንስተዋል።

በዚህም የአስፈጻሚ አካላት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ታይቶ ግብረ መልስም ተሰጥቷል።

ጨፌው የተሰጠው ሀላፊነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደመሆኑም ከአጎራባች ክልል ህዝቦች ጋር በቅርበት ተሰርቷልም ነው ያሉት።

ነገ በሚጀምረው ጉባኤ የስድስት ወራት የክልሉ መንግስት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶችም ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ይፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአዳነች አበበ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.