Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው  ለኮቪድ 19 መከላከል ከ 7 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 27፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አመራር ኤጀንሲ ለኮቪድ-19 መከላከል የሚውል  7 ሚሊየን 36 ሺህ652 ብር  ድጋፍ አድርጓል።

የኤጀንሲው አመራሮች እና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን በማሰባሰብ ድጋፉን ለኮቪድ-19 አሰባሰብ ኮሚቴ  አስረክበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ÷ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ከሚከታተላቸው እና ከሚያስተዳድራቸው የስደተኛ ጣቢያዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከውጭ ሃገር የሚመለሱ ዜጎቻችንን ወደየአካባቢያቸው እስኪሄዱ ድረስ ያለውን አስተዳደር እንዲሁም የውጭ ሃገር ዜጎችን መጠለያና ስንቅ በማቅረብ ትልቅ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር  ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው÷ የሚኒስትሪው ተጠሪ ተቋሞች አንዱ የሆነው ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አመራር ኤጀንሲ የሚደረገውን ወገንን የማዳን ርብርብ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እና የህይወት መስዋዕትነት ከመክፈል አልፈው ከራሳቸው እና ቤተሰባቸው ጉሮሮ በመቀነስ ለወገን ያደረጉት ድጋፍ እጅግ በጣም የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት መጠኑ እየሰፋ የመጣውን ወረርሽኝ ለመከላከል ወገን እርስ በራሱ መደጋገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደጋግፎ መቀጠል እንዳለበት እና ለመንግስትም የሚደረገው ድጋፍ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት የዛሬውም ድጋፍ አነቃቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

,የብሔራዊ ሃብት አሰባሰብ ኮሚቴ አባል እና የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ምስጋኑ አረጋም ድጋፉን በመረከብ ኤጀንሲው ለሰጠው ወገናዊ ጥሪ ምላሽ  ማመስገናቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.