Fana: At a Speed of Life!

“የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን መብራትም እራትም ነው”- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን መብራትም እራትም ነው” ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን በዛሬው እለት ሃይል ማመንጨት ጀምሯል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም ይህ ታላቅ የምስራች ነው ያለው አገልግሎቱ፥ ይህም ከወራት በፊት የተጀመረውን ኃይል የማመንጨት አቅም በማሳደግ የግድቡን ግንባታ ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብሏል።

ከግድቡ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ዕውን ሆኖ ለማየት የሚያስችል ትልቅ ስኬት መሆኑንም አስታውቋል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ይህ ታላቅ የምስራች ነው። ይህም ከወራት በፊት የተጀመረውን ኃይል የማመንጨት አቅም በማሳደግ የግድቡን ግንባታ ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።

ከግድቡ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ዕውን ሆኖ ለማየት የሚያስችል ትልቅ ስኬት ነው።

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የውጪ ሀገራት ድጋፍ በራሱ አቅም የሚሰራው በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው።

የመቻል አቅማችንን የሚያሳይ፣ የልማት ፍላጎታችንን የሚያመላክት፣ የህብረት ስኬታችንን በጉልህ የሚያሳይ ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ ነው። መንግስትም ህብረተሰቡን በማስተባበር፣ ባለሙያዎችን በማሰማራት እና የክትትል እና ድጋፍ ስርዓት በመዘርጋት የግድቡን ግንባታ ሂደት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጓል።

በዲፕሎማሲው በኩልም ከታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር በመነጋገር እንዲሁም የማሳመን ስራ በመስራት የግድቡ ግንባታ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ተደርጓል።

የህዳሴ ግድቡን ግንባታ የሚያከናውኑ ባለሙያዎችም ለ24 ሰዓታት ያልተቋረጠ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም በታሪክ ትልቅ እውቅና የሚሰጠው ብሄራዊ ኩራት ነው፡፡

ለሀገር ልማት የዋለ ያልተቆጠበ ሙያዊ አርበኝነት በመሆን ሁሌም ሲወሳ የሚኖር የህዝብ እና የሀገር ውለታ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎችም የግድቡ ግንባታ የሚከናወንበትን አካባቢ በንቃት በመጠበቅ ታላቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

የአካባቢው የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው ሌት ተቀን አኩሪ የሀገር ዘብነታቸውን እያስመሰከሩ በመሆናቸዉ ክብር ይገባቸዋል፡፡

በዲጂታል ዲፕሎማሲውም በሀገር ውስጥ እና በውጪ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ልጆች በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚነዙ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በመመከት እና በማጋለጥ የኢትዮጵያን እውነት ለአለም ህዝብ እያሳወቁ የግድቡ የግንባታ ሂደት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ላይ የተደረሰው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በሁሉም መስክ እያደረጉ ባሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉን አቀፍ ርብርብ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት ተባብረው የህዳሴውን ግድብ በማጠናቀቅ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆናቸውን በተግባር እንደሚያሳዩ የእስካሁኑ ስኬት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

አፍሪካ በራሷ አቅም መልማት እንደምትችልም ግንዛቤ የፈጠረ አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ የኤሌክሪክ ኃይል ስታመነጭ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የልማት ስንቅ ከመሆኑም ባሻገር ለተቀሩት አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደግሞ የልማት ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡

በተጨማሪም በማገዶ እንጨት መሸከም ወገባቸው የጎበጠ እናቶቻችን እና እህቶቻችንን ቀና አድርጎ መብራት እና እራት በመሆናቸው እሙን ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ልጆች የህብረት ስራና ቁርጠኝነት ይጠናቀቃል፡፡

ልማታችንም ዕውን ይሆናል!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.