Fana: At a Speed of Life!

የሶስቱ ቀናት ፈታኝ ተጋድሎ በብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም አንደበት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳንሻ ከተማ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ አምስተኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር ካምፕ ጊቢ ውስጥ የመከላከያ መኪናዎች በጥይት ተበሳስተው ይታያሉ፡፡

መስታወታቸው ረግፏል፤ዛፎቹም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፤ መጥረቢያ እንጂ የጥይት ውርጅብኝ የቆረጣቸው አይመስሉም።የግንብና ቆርቆሮ ቤቶች እንደ ወንፊት ተበሳስተዋል፡፡የጥይቶች ቀላሃ እንደ ጠጠር ተብትኗል፡፡

ዕለተ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት አካባቢ በዳንሻ ከተማ ያልተጠበቀ፣ አሳዛኝ፣ አስደጋጭ ድርጊት ነው የተፈጸመው፡፡በከተማዋ የሚገኘው የሰሜን ዕዝ የአምስተኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር የተደገሰለትን ጥቃት አያውቅም።በመካናይዝድ ክፍለ ጦሩ ስታፍ ውስጥ የሚሰሩት መደበኛ ስራቸውን ከውነው እንቅልፍ ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ምሽት ግን የትግራይ ልዩ ሀይል አባላት ወደ ካምፑ ዘለቁ፤ ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱን እንደሚፈልጉትና እንዲጠራላችሁ የበር ጥበቃዎችን ይጠይቃሉ።

ጀኔራሉም እንደማይመጡ ሲነገራቸው ተመልሰው ይሄዱና ተጨማሪ ሀይል ይዘው መጥተው በካምፑ ላይ የጥይት መአት ማውረድ ይጀምራሉ፡፡ውስጥ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም በጽናት የመመከት ስራ ውስጥ ገቡ፤ለሶስት ቀንና ሌሊት በጽናት ታገሉ፡፡

አንድ የመከላከያ ሰራዊት የመረጃ ሰራተኛ ወደ ጀነራሉ ጆሮ ተጠግቶ አካባቢውን የትግራይ ልዩ ሀይሎች ከቦታል፡፡ፍላጎት ካለህ ሽማግሌዎቹ ከአካባቢው እናስወጣው ብለው ነግረውኛል፤ ውሳኔህ ምንድነው ሲል ጠየቀኝ ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ፣ የእነሱ ፍላጎት እኔም ወኔዬን ተሰልቤ የሲቪል ልብስ ለብሼ ተደብቄ ወደ አማራ ክልል እንድወጣ አልያም እኔን አታለው እንድያዝ በማድረግ ካምፕ ውስጥና በአቅራቢያው ባለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ለመሰንዘር ያቀዱትን ጥቃት የመከላከልና የመመከት ስራ ለማሰናከል ነው፡፡

በዚህም በቀላሉ ሰራዊቱንና መሳሪያውን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስበው መሆኑን ገለጹልን፡፡

እኔም ምላሼ ሽምግልናውን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን የመረጃ ሰራተኛው ከሽማግሌዎቹ ጋር ለጥሩም ይሁን ለመጥፎ መገናኘት እንደሌለበት አስጠንቅቄ ነገርኩት ።አሁን ይህን ያለኝ ልጅ ቆስሎ ለህክምና ወደ ጎንደር ሄዷል።ሲመጣ ጠይቄ ዓላማቸው ምን እንደነበር የምረዳው ይሆናል፡፡

ተመትቶ ስለነበረ እኔም እንዳልሞት አስቦ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ ብለውናል።

የሶስት ቀን ከበባው በጣም አስቸጋሪ ነበር።24 ሰዓት ተኩስ ነው፡፡ያጠቃሉ እኛ እንከላከላለን፤ይሄዱና ምግብ በልተው ሀይል ጨምረው ያጠቃሉ፤ ሲታኩሱ የነበሩት ልዩ ሀይሎች ወደ ካምፓቸው ሄደው አርፈውና ጥይት ጭነው ይመጣሉ፡፡እኛ ካለንበት ቦታ ውጭ መፈናፈኛ ስፍራ የለንም፡፡

እንደ ቀለበት ዙሪያውን ከበውና ውሃ ፣ምግብ፣ጥይት የለም፡፡ያለችንን ነው በቁጠባ የምንጠቀመው ሲሉ ያብራሩት ጀነራሉ፣እኔም አልፎ አልፎ እንደ ምሽግ ከተጠቀምኩበት ግንብ ቤት እየወጣሁ ለወታደሮቼ ጥይት በቁጠባ ተጠቀሙ እያልኩ አሳስብ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ፡፡እነሱም አላሳፈሩኝም በጽናት ተዋደቁ።

የሰራዊታችን በጽናት የመከላከል ሞራል የሚገርም፣ የሚደነቅና ታምር የሚያስብል ነው ይላሉ፡፡

አርቢጂ፣ቦንብ፣መትረየስ ፤ክላሽ እንደ ዝናብ ቢያርከፈክፉብንም ለሶስት ቀናት ቀንና ሌሊት መክተናል፡፡በፍጹም እንተርፋለን ብለን አላሰብነም ፤ከቻልን እስከ መጨረሻው እንከላከላለን ፤ካልቻልን ደግሞ በመጨረሻ ላይ ራሳችንን እናጠፋለን የሚል አቋም ነበርን፡፡

ግን በእግዜአብሄር ቸርነት፤በመከላከያ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽነት ቀለበቱ ተሰብሮ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል ብለውናል፡፡ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም፡፡

ድርጊቱ የሚያሳዝን ነው፤ በህወሓት ከሀዲ ቡድን እንዲህ አይነት ጥቃት ይፈጸምብናል ብለን አስበን፤አልምንም አናውቅም የሚሉት በሰሜን ዕዝ የአምስተኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ሙሉዓለም አድማሱ፤ ምክንያቱም ከኢትዮ-ኢርትራ ጦርነት ጀምሮ ትግራይ መሬት ነው እየኖርን ያለው።ህዝቡን መሪዎቹንም በደንብ እናውቃቸዋለን ብለዋል፡፡

“አብረህ እየበላህ እየጠጣህ፣ተዋልደህ ተጋምደህ፤ ትዳር መስርተህ ፣ልጆች ወልደህ፤ቤተሰብ ሆነህ በፍጹም ጥቃት ሊሰነዝርብኝ ይችላሉ ብለህ አታስብም፤ሆኖም ያልታሰበው ተፈጸመ፤ያልተጠበቀው ሆነ “ሲሉ በትግራይ ክልል ልዩ ሀይል የተሰነዘረባቸውን ጥቃት አሳዛኝ ሲሉ ይገልጹታል።

ኩርፊያና የተለያዩ መገለጫዎች ይታያሉ ፡፡ይህን ተከትሎ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም ደፍረው መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ውስጥ ገብተው ያጠቃሉ ብለን አላሰብንም።

ምክንያቱም ወንድምህ ሊያኮርፍ ይችላል እንጂ ያጠቃኛል፤ይገለኛል ብለህ ፈጸሞ አትገምትም የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራሉ፤ግን የትግራይ ልዩ ሀይሎች ዕለተ ማክሰኞ 25ቀን 2013ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ያለምንም ርህራሄ ዙሪያውን እንደ ቀለበት ከበውን አጠቁን ፣አጠቁን እኛም በጽናት ተከላከልን፤መከትን ብለዋል፡፡

የህወሓት ቡድን ዓላማ የመከላከያ ሰራዊትን መድፎች፣ ታንኮች፣ብረት ለበሶችን መንጠቅና መከላከያን ማፍረስ ነው፡፡ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም ፤በራሳችን መሳሪያ ተመልሰው እኛን ለመውጋት ነበር ዕቅዳቸው፡፡ይህ አልተሳካላቸውም፡፡እኛም በያለንበት በጽናት ተዋግተን መክተናል፡፡

አሁን እነሱ ባሰቡት ሳይሆን እኛ ባሰብነው መንገድ እየሄደ ነው፡፡በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱ ይቋጫል ብለን እናስባለን ሲሉ ገልጸውልናል።
ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም አንድ የሚገርማቸው የሚደንቃቸው ነገር አለ፡፡”እኔ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊና ተራ ጄነራል ነኝ፣በአንድ ክላሽ ጥይት ግፋ ቢል ደግሞ በስናይፐር መግደል ይችላሉ፤ ግን የጭካኔያቸው ጭካኔ አርቢጂ ነው የተኮሱብን ።

አርቢጂ የሚባለው መሳሪያ ደግሞ ለታንክ ወይም ለጠንካራ ምሽግ ነው የሚተኮሰው፤የእኔን ቤት ለማፍረስ ግን አርቢጂ ነው የተኮሱት ሲሉ የከሀዲው ቡድን የጭካኔ ጥግ ምን ያህል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እኔ ብሞትም ቤቱ የእነሱና የህዝቡ ንብረት ነው። ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ጸጥታ ለቆምኩ፣ለአገር ሉዋላዊነትና ለህዝብ ሰላም ውድ ህይወቴን ለመስጠት በተሰለፍኩ የክህደታቸው፣የክፋታቸው ጥልቀት እኔን በአርቢጂና በቦንብ ነው ያጠቁት ሲሉ የድርጊቱን ክፋት ገልጸውታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ እየኖረ ያለ፣ለህዝቡ የልማት ስራዎች ወደ ኋላ የማይል፣ በማህበራዊ ድጋፎች የሚሳተፍ፣ ሁልጊዜ በየዓመቱ ለአቅመ ደካሞች የሚያርስ፣ የሚያርም፣ የሚያጭድና አንበጣ የሚከላከል ነው።

በትምህርት ቤቶች፣በጤና ጣቢያዎች፣በመንገድ ግንባታዎች በሚሳተፍ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም የህወሓት ቡድን እወክለዋለሁ ቆሜለታለሁ ለሚለው ህዝብ ደንታ እንደሌለው ያሳያል ይላሉ፡፡

የአገሩን ዳር ድንበር የሚጠብቀውን፤የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ስብስብ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ለማውድምና ለማጥፋት ነው ጥቃቱን የሰነዘሩት ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በኋላ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቢሰብኩ፣ ቢለፈልፉ፣ ቢቀሰቅሱ ማን ጀሮ ይሰጣቸዋል ፡፡

ምክንያቱም ጥቃቱን በጽናት ለመመከት የተዋደቁት ከኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተወጣጡ ወታደሮች ናቸው ብለዋል፡፡

ጀኔራሉ በ1980ዓ.ም በወቅቱ ኢህዲን ተብሎ የሚጠራውን ትግል የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ከዚሁ ዓመት ጀምሮ ደርግ እስኪደመሰስ ድረስ በተደረጉ ውጊያዎች ተሳትፈዋል።ቆቦ አካባቢ በተካሄደው ሰላም በትግል ኦፕሬሽን፤ሰሜን ሸዋ መራኛ፣ ጁሁርና መራቤቴ አውድ ውጊያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በጎጃም ደጀን፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ ጅማ፣ ቡሌሆራ (አገረ ማርያም) ሞያሌ ድረስ በዘለቀው አውድ ውጊያ ተሳትፈዋል፡፡ በሀረርም ጸረ ሰላም ሀይሎችን በመከላከልና በማጥቃት ዘመቻ ተሳትፈዋል፡፡ በሩዋንዳ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በ1986ዓ.ም ግድጃቸውን በስኬት አጠናቀው ተመልሰዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲቋቋምም 20ኛ ክፍለ ጦር መድፈኛ ብርጌድ አንደኛ ሻለቃ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮ-ኢርትራ ጦርነትም ትምህርታቸውን አቋርጠው በመሄድ ብርጌድ አዛዥ በመሆን በጾረና፣ በባድመ፣ በሽራሮ አዲኋላ ግንባር ተሳትፈዋል፡፡

አሁንም በዳንሻ ከተማ በትግራይ ልዩ ሀይል የተካሄደውን ከበባና ሶስት ቀናት የዘለቀ ጥቃት ወስን ወታደሮችን መርተውና አዋግተው በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ዕገዛ መከላከሉን በድል አጠናቀው የማጥቃቱን ተልዕኮ በድል እየተወጡ ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተወሰደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.