Fana: At a Speed of Life!

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት እየቀየረ ነው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት በመቀየርና ወደ ዘላቂ ልማት እንዲሸጋገሩ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና እንደነበረው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ሁለተኛው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ዛሬ በደሴ ከተማ ይፋ ተደርጓል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክትን ዛሬ በደሴ ከተማ ይፋ አድርገዋል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በከተማ በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት በመቀየርና ወደ ዘላቂ ልማት እንዲሸጋገሩ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና እንደነበረው አቶ ደመቀ በዚህ ውቅት ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ አቅመ ደካማ  ዜጎችን መርዳት ከልቦና ጋር የሚያስታርቅና የአዕምሮ እርካታ የሚሰጥ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

“ስንተባበር እና ስንከባበር የምንፈልጋትና የምንኮራባት ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን” ያሉት አቶ ደመቀ፥ በሁለተኛው ዙር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የአቅመ ደካሞች ሕይወት በዘላቂነት እንዲለውጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው፥ “መንግስት ድህነትን ለመቀነስ የሚያደርገውን ትግል ሁሉም ባለድርሻ አካል ሊደግፍ ይገባል” ብለዋል።

የመጀመሪያው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን የሥራ ባህል ያሳደገና የከተሞችን ገጽታ የቀየረ መሆኑንም አንስተዋል።

በሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከቀድሞው ተሞክሮ በመውሰድ አፈጻጸሙ የተሻለ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን ለማብሰር በደሴ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የአማራ ክልል አፈ ጉባኤ፣ የክልል መስተዳድሮች እና ምክትል መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እንዲሁም የተለያዩ ከተምች ከንቲባዎችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.