Fana: At a Speed of Life!

የወላይታ ልማት ማኅበር በአዲስ አበባ የባህል ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ልማት ማኅበር በአዲስ አበባ የባህል ማዕከል እንዲገነባ ከከተማ አስተዳደሩ መሬት ተሰጠው።

የወላይታ ልማት ማኅበር የ20 ዓመት የልማት እቅዱን ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ በአዲስ አበባ አስተዋውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ የልማት አርበኝነቱን ያስመሰከረ አንጋፋ ማኅበር መሆኑን ገልጸዋል።

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ብሎም በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።

ለህዳሴ ግድብ፣ ለመከላከያና ለተማሪዎች ምገባ መርኃ ግብር የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን እንዳሳየም ገልጸዋል።

በመሆኑም የልማት ማኅበሩ በከተማዋ የባህል ማዕከል ለመገንባት የጠየቀውን ጥያቄ በመቀበል ለግንባታ የሚሆን መሬት ማዘጋጀቱን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ማኅበሩ ለሀገርና ህዝብ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ÷የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በማመስገን የባህል ማዕከሉን ግንባታ በፍጥነት እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።

ማኅበሩ ዛሬ ባስተዋወቀው የቀጣይ 20 ዓመት እቅድ በ8 ቢሊየን ብር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ከእነዚህ የልማት ሥራዎች 85 በመቶው ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠርና ለሰው ሃብት ልማት የሚውል ሲሆን ቀሪው ለሌሎች ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች ይውላል ብለዋል።

በተለይም የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የዲጂታል የትምህርት ሥርዓትን የማስፋፋትና የወላይታ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ማቀዱን አክለዋል።

በወላይታ ሊቃ ብቻ የሚገኘውን ሞዴል ትምህርት ቤትም ወደ አስር ወረዳዎች የማስፋትና ሌሎችም በትምህርት ዘርፍ ያሉ የማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ፣ በእንሰሳት ሃብት፣ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና እንክብካቤ እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ሥራዎችን ለመስራት ውጥን እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ማኅበሩ እቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየርም የአጋር አካላት ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዶክተር እንድሪያስ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.