Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ከ12 ሺህ በላይ ለሆኑ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል ከ12 ሺህ በላይ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጎላቸው ከማረሚያ መውጣታቸውን የደቡብ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
 
የክልሉ ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ሙሉሰው ዘውዴ በሰጡት መግለጫ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በመደበኛና በልዩ ሁኔታ ከተለያዩ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች 12 ሺህ 553 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
 
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ እንዳሉት በመደበኛ መንገድ የይቅርታ ተጠቃሚዎችን መረጣና ምልመላ መስፈርት መሰረት ባደረገ መልኩ በአግባቡ የታረሙ፣ የታነጹና መልካም ስነ ምግባር ያሳዩ 3 ሺህ 519 ወንድና 119 ሴት እንዲሁም 4 የእስራት ቅነሳ የተረገላቸው በድምሩ 3 ሺህ 642 ታራሚዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
 
አቶ ሙሉሰው የክልሉ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርና ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ በልዩ ሁኔታ 8 ሺህ 601 ወንድና 310 ሴት በድምሩ 8 ሺህ 911 ታራሚዎች እንዲፈቱ አድርጓል ነው ያሉት።
 
በተለይም ደግሞ ነፍሰ ጡሮች፣ ህጻናት ያላቸው፣ ልዩ ልዩ ህመም ያለባቸው፣ እድሜያቸው የገፋ፣ ከ18 አመት በታች የሆኑና አመክሯቸው የተቃረበ ግለሰቦች እንዲወጡ መደረጉን አቶ ሙሉሰው ጠቁመዋል ።
 
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ሙሉሰው ከህብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ጊዜም መልካም አርኣያ ሊሆኑ ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
በሌላ ወንጀል የሚሳተፉ ከሆነም ይቅርታቸው ተሰርዞ በህግ የሚጠየቁበት አግባብ እንዳለም ገልጸዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.