Fana: At a Speed of Life!

ረመዳን የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት፣  የመተሳሰብና የመደጋገፍ  ወር ነው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ኢትዮጵያውያን ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ቀናይነት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል፣ በይቅር ባይነት አልፈው ሀገራቸውን አጽንተው ለማቆየት መቻላቸውን አውስተዋል፡፡

በዚህ የረመዳን ቅዱስ ወር የጀነት (የገነት) በሮች የሚከፈቱበት፣ የጀሃነም (የገሃነም) በሮች የሚዘጉበት፣ ሠይጣንም የሚታሰርበት፣ መልካምነት ጎልቶ የሚሠፍንበት፣ የፈጣሪ ምሕረት የሚበዛበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ረመዳን ክፉ ማሰብና ክፉ ማድረግ ቀርቶ የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ  ወር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የወሩ ፍጻሜ እና የጾም ፍቺ የሆነችው ዒድ አልፈጥር ደግሞ የበጎ ነገሮች ሁሉ ማሠሪያ ተደርጋ ትወሰዳለችም ነው ያሉት፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በዒድ አልፈጥር በዓል ለተቸገሩት ዘካን በማውጣት፣ እንዲሁም ምስኪኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ለተቸገሩት ዘካትል ፊጥር (ምጽዋት) በመስጠት፣ የደከመን በመደገፍ የሚያሳልፉት ከፈጣሪ ምሕረትንና ጽድቅን ለማግኘት ነው ብለዋል፡፡

ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገርም አባቶቻችን ችግሮቻቸውን ሲፈቱበት የቆየውን የፍቅርና የመቻቻል መንገድ መከተል ይኖርብናልም ነው ያሉት፡፡

ሁላችንም የእምነቶቻችን አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት መጓዝ ከቻልን የከበደው ይቀላል፣ የጨለመው ይበራል፣ ውስብስቡና ውል ያጣው ችግራችን ሁሉ መፍትሔ ያገኛልም ብለዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.