Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በመስኖ የሚለማ 10 ሚሊየን ሄክታር መኖሩ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ 10 ሚሊየን ሄክታር በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እንዳላት በጥናት መለየቱን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን ጠቅሶ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተቋሙ በትጋት እንዲሠራ የውኃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ እንዲሁም አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡

ከጥናትና ዲዛይን ሥራ አንጻርም ፕሮጀክቶችን በዕቅዱ መሰረት ከማከናወን አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖሩን አንስቷል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ተቋሙ በትኩረት እንዲሠራ ኅብረተሰቡ መጠየቁንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ የፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ዲዛይን ሂደት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች መዘግየትም ምክንያቱ የዲዛይን ሠነድ ችግር መሆኑን ጠቅሰው÷ ወደ ግንባታ ለመግባት በጀት እየተጠባበቁ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ሀገራዊ የዲዛይን ሠነድ ኮድ እንዲዘጋጅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን አጠቃላይ የመስኖ አቅም መረጃና ቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫ ጥናት በማድረግ 10 ሚሊየን ሄክታር በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እንዳላት ማወቅ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በየሻምበል ምኅረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.