3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ ከተማ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሐሳብ ለ5 ቀናት በድሬዳዋ የሚካሄደው 3ኛው ዙር ንቅናቄና የአምራች ኢንዱስትሪዎች ዐውደ ርዕይና ባዛር ተጀምሯል።
3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት የድሬዳዋ ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈትህያ አደንና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የተከፈተው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤት የሆኑ ተኪ ምርቶችና በድሬዳዋ የተገጣጠሙ መኪኖችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፥ ኢንዱስትሪዎችን አበረታተዋል።
ከ40 በላይ የአምራች ኢንዱስትሪዎችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተሳተፉበት ዐውደ-ርዕይ ላይ ኢንዱስትሪዎቹ የተለያዩ ተኪ ምርቶቻቸውን ለእይታ አቅርበዋል ነው የተባለው።
ንቅናቄው በኮሌጆችና ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ የተለያዩ የፈጠራ ማሽኖችን እና ሌሎች የፈጠራ ውጤቶችን በማቅረብ የተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።