Fana: At a Speed of Life!

 “ኢትዮጵያ፤ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ኢትዮጵያ፤ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” የሚል ርዕስ ያለው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል።

የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ 2013 እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር ነው ተብሏል።

የዕቅዱ ዓላማዎች ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት፣ ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የሥርዓታት ለውጥ ማምጣት፣ የሴቶች እና የወጣቶችን ፍትሐዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ መሪነት ማረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚያም ባለፈ ሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ዕድገት እንዲኖራቸው መሠረት የሚሆኑ አምስት ምሦሦዎችም ያሉት ይህ ዕቅድ፣ ያሉ ጥንካሬዎችን እና ዕምቅ ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በተለይም የኢነርጂ ዘርፍን የሚመለከተው ዕቅድ፣ ለአብዛኛዎቹ የልማት ፍላጎቶች እንዲሁም ለሁሉም ዘርፎች ኢነርጂ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመሪ ልማት እቅዱ ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ የነፍስ ወከፍ ገቢን በአማካይ 8 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ግብ መቀመጡ ተገልጿል።

ከዚያም ባለፈ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘውን ህዝብ ቁጥርም አሁን ካለበት 19 በመቶ በ2022 ወደ 7 በመቶ ለመቀነስ ይሰራል ተብሏል ።

የልማት እቅድ የትኩረት መስኮችም ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ከተማ ልማት፣መሰረተ ልማት፣የሰው ሀብት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ ዘላቂ የልማት ፋይናንስ መሆኑ ተመላክቷል።

የ10 ዓመት ዕቅዱ በውጤታማነት እንዲፈጸም የፌደራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት ÷ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች እና ኢንቨስትመንቶች በሙሉ የነፍስ ወከፍ ገቢን ለማሳደግ አስተዋጽዖ እንዲኖራቸው ማስቻል፣ ፕሮጀክቶች ጥራት እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ ማንኛውም ወጪ በአግባቡ በጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እና ‘ድህነትን ከመዋጋት’ ትርክት ወጥቶ ባለ ብዙ ገጽ ብልጽግናን ወደ መገንባት መሸጋገር ይገባል ተብሏል።

በዓላዛር ታደለ

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.