ለፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የደንብ ልብስ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ስምምነቱን የተፈራረመው ከዶንግ ፋንግ ሲሊፒንግ ኃ/የተ/የግ ማህበር ጋር መሆኑም ተገልጿል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ÷ስምምነቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የደምብ ልብስ የፖሊስ ሠራዊቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለግዳጅ ሲሰማራ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈፀም እንዲያስችለው የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ አልባሳት እንዲዘጋጁ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት መስዋዕትነት እየከፈለ ሀገሩን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚጠብቅ በመሆኑ እና በተሰማራበት አካባቢ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ አልባሳቱን የማቅረብ ሂደቱን በማፋጠን ለሠራዊቱ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን ድርጅቱ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ማሳሰባቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የዶንግፋንግ ሲፒኒንግ ፕሪንቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተወካይ ፋሚንግ ዘኡ በበኩላቸው÷ድርጅታቸው በገባው ውል መሠረት አልባሳቱን በጥራት አምርቶ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ለፌደራል ፖሊስ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡