Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በሁለት ዙር በተካሄደ የፅዳት ዘመቻ 25 ሺህ ቶን ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በሁለት ዙር በተካሄደ የፅዳት ዘመቻ 25 ሺህ ቶን ደረቅ ቆሻሻ እና 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ማጽዳት መቻሉ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በአዲስ አበባ ፅዱ ያልነበሩ የተለያዩ አካባቢዎችን በማጽዳት አሁን ውብና ፅዱ ማድረግ ተችሏል ያሉ ሲሆን ÷እነዚህን ውብ ስፍራዎች እንደተዋቡ እንዲቆዩም ፅዳቱ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት የአካባቢያችንን ቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ልናፀዳ ይገባል ያሉት አቶ ጥራቱ የኢትዮጵያንም ጠላቶች ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር በመሆን እናፀዳለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ከተማዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ በጀመረው የፅዳት ዘመቻ 25 ሺህ ቶን ደረቅ ቆሻሻ እና 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ማፅዳት እንደተቻለ የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ይህንን የፅዳት ዘመቻ በማስቀጠል ዛሬ ሶስተኛውን ዙር የፅዳት ዘመቻ ማስጀመሩ ታውቋል፡፡

በሶስተኛው ዙር የፅዳት ዘመቻ ጳጉሜን አምስቱን ቀን ጨምሮ በቀጣይ በአዲስ ዓመትም “በአዲስ ዓመት ፅዱና ውብ አዲስ አበባ” በሚል መሪ ቃል እንደሚቀጥል ዶክተር እሸቱ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ለፅዳት አምባሳደሮችና ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.