Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ የሚባሉ ሰዎች ራስ ለማጥፋት ተጋላጭ መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወንድ አያለቅስም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ወጣት ወንዶች ከሌሎች የበለጠ ራሳቸውን ለማጥፋት ቅርብ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመላከተ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች በተለይም ጠንካራ የሚባሉ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ህወታቸውን ለማጥፋት ቅርብ መሆናቸውን ያሳያሉ።

ለዚህ ደግሞ ወንዶቹ ስሜት ውስጥ ሲገቡ በአብዛኛው መሳሪያ መጠቀምን አማራጭ ማድረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት መንፈሰ ጠንካራ የሆኑ ሰዎች በዚህ ረገድ ዋነኛ ተጋላጭ ናቸው።

ይህ መረጃ ከሰውነት ጥንካሬ ጋር ተያይዞ ያለው ልማዳዊ አመለካከት ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚል ጥያቄን ማስነሳቱን ዳንኤል ኮልማን የተባሉ ተመራማሪ ይገልጻሉ።

ተመራማሪው ስሜታቸውን የማያስተናግዱ፣ የሰውን ድጋፍ የማያገኙ እና ቁጡ የሆኑ ሰዎች ራስን ለማጥፋት ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።

በፈረንጆቹ 1995 መካሄድ የጀመረው ጥናት 20 ሺህ 700 አሜሪካውያን ታዳጊዎችን ያሳተፈ ሲሆን እስከ 2014 ድረስም ጠንካራ የሚባሉ 22 ሰዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል።

ራሳቸውን ካጠፉት መካከል አንድ ሴት ብቻ ራሷን ማጥፋቷ ነው የተነገረው።

ጥናቱ ከሰውነት ጥንካሬ ጋር የተያያዘ አመለካከትን የሚያዳብሩ ወጣቶች ከሌሎቹ ወንዶች አንፃር በሁለት እጥፉ ራሳቸውን የማጥፋት ልምድ እንዳላቸው አመላክቷል።

አሜሪካውያንን ብቻ ዋቢ ያደረገው የጥናት ውጤት ላይ ተጨማሪና ሰፋ ያለ ምርምር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ባለሙያው የገለጹት።

ምንጭ፦ www.webmd.com/

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.