Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው በቆይታው ጥሩ ጊዜን እንደሚያሳልፍ እምነታችን ነው- የሶማሌ ክልል መንግስት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሀገር ወዳድ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል እና ወደ ክልሉ የሚመጡትን ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን የሶማሌ ክልል አስታወቀ።

ይህን ታሪካዊ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት አስመልክቶ የሶማሌ ክልል መንግሥት መግለጫ አውጥቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ ታሪካዊውን “የጉዞ ወደ ሀገር ቤት” ምላሽ በመስጠት ከተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሀገር ወዳድ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጅቷን ጨርሳ ልጆቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች ብሏል።

መግለጫው በሶማሌ ክልል ያለውን አስተማማኝ ሰላም ተከትሎ ባለፉት ሦስት አመታት በሰፈነው ለውጥ በርካታ መሰረተ ልማቶች መሰራታቸውን ገልጿል።

ይህም በክልሉ ከተሞች ባሉ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ መንገዶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና የቱሪስት መዳረሻዎች ዳያስፖራው በቆይታው ጥሩ ጊዜን እንደሚያሳልፍ እምነቱ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታት በሶማሌ ክልል በሰፈነው ልማትና መረጋጋት ክልላችን የተለያዩ ዳያስፖራዎች መዳረሻ በመሆን አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ያለው መግለጫው፥ ወደ ክልሉ በየጊዜው የሚመጡ እንግዶች በቆይታቸው ጥሩ መስተንግዶና አገልግሎት እንዲያገኙ መንግሥት ከህዝቡና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛልም ነው ያለው።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ የሚመራው የክልሉ መንግስት ባለፉት ሦስት አመታት ካስመዘገባቸው ድሎች መካከል ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተጠቃሽ ሲሆን፥ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በጤና፣ በቱሪዝም እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ መነቃቃት በመፈጠሩ የተለያዩ ዳያስፖራዎች በፈለጉት የስራና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ የክልሉ መንግሥት ባመቻቸው ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በርካቶች መዋእለ ንዋያቸውን አፍስሰው ተጠቃሚ መሆን መቻሉን መግለጫው አንስቷል።

“ውድ የዲያስፖራ ማህበረሰባችን፣ የምስራቋ ፀሀይ በሆነችው ጅግጅጋ ከተማና ሌሎች ከተሞች ስትመጡ የሶማሌ ክልል ህዝብ የሚታወቅበትን እንግዳ ተቀባይነት ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቹዋል፤ በሚኖራችሁ ቆይታም እንግዳነት ሳይሰማቹ ልክ እንደቤታቹ በክልላችን ደማቅ ጊዜን እንድታሳልፉ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል።

በሶማሌ ክልል ባለው አስተማማኝ ሰላም ምክንያት የኢንቨስትመንት አማራጮች በተለይ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በቁም እንስሳትና ተዋፅኦ፣ በሆቴልና በንግዱ ዘርፍ ያሉትን እድሎች በሚኖራቸው ቆይታ ተመልክተው በፈለጉት የኢንቨስትመንት መስክ ለወደፊት እንዲሰማሩ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸቱን ገልጿል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ብትሆንም የህዝቡና ሀገር ወዳድ ዳያስፖራዎች በከፈሉት መስዋዕትነትና ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት እያደረጉ ባለዎ ድጋፍ ኢትዮጵያ ቀና እንዲትል አድርጓል ያለው መግለጫው፥ “ውጭ ሀገር ሆናችሁ ወደ ሀገራቹ የምትልኩት ገንዘብ እና ሀብት የኢኮኖሚያችን ምሰሶ እንደሆናችሁ እናምናለንም” ነው ያለው።

በሌላ በኩል ሀገር ለማዳን በሚደረገው ትግል ሁሉ የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግሥት ተጋድሎ እያደረገ መሆኑን በማንሳት፥ ሰፊውን ድንበር ከፀረ ሰላም ኃይሎች በጀግናው የክልሉ ልዩ ሀይል አማካኝነት በንቃት እየተጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ፈተናዎች በበዙበት ወቅት በክልሉ የመኸርና የበልግ ወቅት ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ በመከሰቱ ህዝብና እንሰሳትን ከድርቁ ለመታደግ የክልሉ መንግሥት እያደረገ ያለውን ርብርብ ዳያስፖራው ወደ ክልሉ ሲመጣ እንደወትሮው ሁሉ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ ማቅረቡን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.