Fana: At a Speed of Life!

የጦርነትን ሀሳብ በማምከን ወደ ሰላም መምጣትና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ከወጣቱ እንደሚጠበቅ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  የጦርነትን ሀሳብ በማምከን ወደ ሰላም መምጣትና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አበቤ ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የነበረባትን የስነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነቶችና በህዝቦቿ አንድነትና ጥንካሬ አሸናፊ ሆና ተወጥታዋለች ብለዋል፡፡

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመበታተን በተለያዩ መንገዶች ጥረት የሚያደርጉ የውጭ ሀይሎች የሚቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉም ነው የተናገሩት፡፡

ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈለን የህይወት መስዋትነት በማሰብ ወጣቶች ለሃገር አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ጦርነቱን አቁመን ወደ ሰላም መምጣታችን በእውቀት ላይ የተመሰረተና የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የዜጎች መብት እንዳይጣስ ህግና ስርአትን መንግስት በበላይነት የሚመራ በመሆኑ ወጣቱ ከመንግስት ጎን መሆን ይገባል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ወጣቱ ከጦርነት በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በጋራ በመወጣት የሀገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ፥ ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ጦርነት በድል የተወጣችበት ማግስት ላይ እንደመገኘታችን ከጦርነቱ በኋላ የተለያየ አጀንዳ በሚኖራቸው ቡድኖች ሀገርን የማተራመስ ተግባራት ሊታዩ ስለሚችሉ ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም በንቃት የማስጠበቁን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እንደገለጹት የአዲስ አበባ ወጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር በጋራ ለሀገሩ የከፈለው መስዋትነት የማይረሳ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በማቋቋምና የተጎዳውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚም ይሁን በስነ-ልቦናም በመደገፍ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም እናስጠብቃለን ማለታቸውን ከአስተዳደሩ ፕረስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.