የኦሮሞና አማራ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሞና አማራ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው ሁለተኛው የጋራ መድረክ በዜጎች ደህንነት ላይ ልዩነትን በማጥበብ የጋራ ጉዳዮችን ይዞ መሄድ በሚል ሃሳቦች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት የመድረኩ ተወያዮች በተግባቡባቸው ሀሳቦች ላይ ባለ አምስት ነጥብ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡
የሁለቱ ብሄር ፖለቲከኞችና ምሁራን በሁለቱ ህዝቦች የጋራ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ ሀሳቦችን ይዞ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ተገልጿል።
በምክክሩ ማጠናቀቂያ ላይ የጋራ የአቋም መግለጫዎች አውጥተዋል።
የአቋም መግለጫዎቹ፡-
• ኢትዮጵያ የብዙ ብሄሮችና ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶችና የፖለቲካ አመለካከቶች ሀገር መሆኗን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያለባት እንድትሆን ተስማምተናል ፡፡
• ሁለቱ ህዝቦች ሰፊ የሆነ የጋራ መስተጋብርና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው መሆናቸውን ተገንዝበናል፤
• ሁለቱ ህዝቦች የጋራ አኗኗር ና አሰፋፈርን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሰላምና መረጋጋት መሰረታዊ መብቶችን ማረጋገጥ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን ተረድተናል፤
• ዝርዝር ታሪካዊ ጉዳዮችን ለአጥኚዎች በመተው በሚያግባባን ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተግባባተናል፤
• ይህ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ሊሂቃን የተጀመረው ውይይት ደረጃ በደረጃ እንዲቀጥልና እያዳበሩ ለመሄድ በውይይታችን ተግባብተናል በማለት የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት፤ በቀጣይም በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ መታቀዱ ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።