Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ካቢኔው በመጀመሪያ የተወያየው÷ የክልሉን ደረጃ የሚመጥን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተሟቶለት በተዘጋጀው የመሥተዳድር ምክር ቤት እና ቤተ-መንግሥት ሕንጻ ግንባታ ዲዛይን ላይ ነው፡፡

ከውይይቱ በኋላም በዲዛይኑ ላይ የሚጨመሩና የሚታረሙ ጉዳዮች ተካተው ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

ዲዛይኑ የመሥተዳድር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ ቤተ-መንግሥት እና ወደ ክልሉ የሚመጡ ከፍተኛ አመራሮች የሚያርፉበት የእንግዳ ማረፊያን ማካተቱ ጸገልጿል፡፡

እንዲሁም የሌማት ቱርፋት ሞዴል ሰርቶ ማሳያ አተገባበር መመሪያን ካቢኔው ማጽደቁን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

መመሪያው የሌማት ቱሩፋት መርሐ-ግብር በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በጥራት እንዲተገበር ለማስተማሪያነት የሚያግዝ ሞዴል ሰርቶ ማሳያ ማቋቋምን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የመስኖ ልማት ስራን ለማገዝ በኡራ ወረዳ ቁሽመንገል ቀበሌ በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ለሚገነባው የሶላር ፓምፕ ግንባታና ተያያዥ ስራ የሚውል 7 ሚሊየን 945 ሺህ 148 ብር በጀት ጸድቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.