Fana: At a Speed of Life!

በሪጅኑ በተፈፀመ ሥርቆት 2 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መውደቃቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለገጣፎ – ቃሊቲ በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች መውደቃቸውን የማዕከላዊ አንድ ሪጅን አስታወቀ፡፡

የሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመርና ፋይበር ኦፕቲክስ ሥራ አስኪያጅ አቶ በሱፈቃድ በቀለ እንዳስታወቁት÷ በመስመሩ ላይ ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት አካባቢ በሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት ተፈፅሟል፡፡

የተፈፀመው ሥርቆት የግሪድ ሥርዓቱን በመረበሽ በለገጣፎና ቃሊቲ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የኃይል መቆራረጥ ማስከተሉን ገልፀዋል፡፡

የወደቁ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን ጠግኖ ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት የአንድ ወር ጊዜ ያስፈልጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ÷ በመስመሩ አማካኝነት ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ኃይል ለማግኘት ወደ ፈረቃ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በሁለቱ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የተፈፀመውን ሥርቆት መልሶ ለመተካት ኃይል በመቋረጡ የሚታጣውን የኤሌክትሪክ ምርት ሽያጭ ሳይጨምር ተቋሙ እስከ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ኪሳራ እንደሚደርስበት ጠቅሰዋል፡፡

የሪጅኑ የጥገና ባለሙያ አቶ ሰይድ አስማማው በበኩላቸው÷ በአካባቢው የሚፈፀመው ተደጋጋሚ ሥርቆት መደበኛ የጥገና ሥራዎችን ከማስተጓጎሉም በላይ ተቋሙን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከቃሊቲ – ለገጣፎ በሚያልፉ የኃይል ተሸካሚ ምሰሦዎች ላይ ስርቆቱ እጅግ የከፋ ነው ያሉት ባለሙያው አንድ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ እስከ 8 ጊዜ በሌቦች እንደተሰረቀ መግለጸቸውን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡

ማህበረሰቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅ እና የጸጥታ አካላትም ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ በማቅረብ አስተማሪ ቅጣት እንዲወሰድባቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.