Fana: At a Speed of Life!

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መረጃ የመለየት ሥራ ተሠርቷል- የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው በሰሜን ሸዋ ዞን ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መረጃ የመለየት ስራ ተሠርቶ ለክልሉ መንግስት መላኩን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው መሰለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ መረጃ የመለየት ስራ ሰርተን ለክልሉ መንግስት ልከናል፤ የአማራና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ተነጋግረው አፋጣኝ መፍትሄ ይሰጡታል ብለን እጠብቃለን ብለዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ጊዜያዊ ጣቢያዎች የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከ51 ሺህ በላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በደብረ ብርሃን ከተማ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ ያህሉ በከተማው ባሉ የተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ቀሪዎቹ በዞኑ ባሉ 13 ወረዳዎች እንደሚገኙ እና የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ዜጎችም የመኝታ ቦታና የአልባሳት ድጋፍ ለማግኘት መቸገራቸውን ነው ኃላፊው ጨምረው የገለጹት፡፡
አሁንም ተፈናቃዮች በየቀኑ ወደ ዞኑ እየገቡ መሆኑን የገለጹት አቶ አበባው÷ ለእነዚህ ዜጎች የሚሆን የመጠለያ ጣቢያ ለመገንባት ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጋር ቦታ የማመቻቸት ስራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
ለመጠለያ ጣቢያው ግንባታ እና ለሌሎች የመሰረት ልማት ግንባታዎች ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር ስምምነቶች እየፈፀምን ነው ያሉት ኃላፊው÷ በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ዜጎች በርካታ ድጋፎችን የሚፈልጉ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአበበ የሸዋልዑል
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.