በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ።
የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና የስፖርት ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች አቀባበል አድርገውለታል።
ለልዑካን ቡድኑ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ የአበባ ጉንጉን የተበረከተ ሲሆን፥ የመከላከያ ማርሽ ባንድ እና የሃገር ፍቅር ቴአትር ቡድን የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎች በማቅረብ አቀባበሉን አድምቀውታል።
በመቀጠልም ቡድኑ በተመረጡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በቱሪስት አውቶቡስ የሚዘዋወር ሲሆን፥ በሸራተን አዲስ ወደተዘጋጀው የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት የማበርከት ስነ ስርዓት እንደሚኖር ተገልጿል።
የቤልግሬድ 2022 የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናን ኢትዮጵያ በ9 ሜዳሊያ ከአለም አንደኛ በመሆን ውድድሩን ማጠናቀቋ ይታወቃል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የሩጫ ዓይነቶች በሁለቱም ፆታ 4 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሃስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው ማምጣት ችለዋል፡፡
ይህ ውጤትም የኢትዮጵያ ከፍተኛው የአለም የቤት ውስጥ ውድድር ውጤት ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በቤልግሬድ 2022 የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አሜሪካ እና ስዊዘርላንድ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡