Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው በ2013 ዓ.ም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2013 ዓ.ም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ÷ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገር እድገት መሰረት የሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚፈልቁበት፣ የሀገሪቱን መጻዒ እድል የሚወስኑ ትውልዶች የሚቀረፁበት በመሆኑ የተቋሙን አቅም መገንባትና ተዓማኒነትን ማሳደግ ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው ÷ ተቋማትን ከመገንባትና በቴክኖሎጂ ከማዘመን አንጻር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
 
የትምህርት ዘርፉን ከፖለቲካ አመለካከት መነጠልና የእነዚህን ተቋማት ተዓማኒነት ለመሸርሸር የሚደረጉ እንቅስቀሴዎች ተገቢ አለመሆናቸውን ነው የተናገሩት።
 
የምክር ቤቱ አባላት ከየመጡባቸው የምርጫ ክልሎች በማህበረሰቡ ለተነሱ የፈተና አሰጣጥና እርማት ሂደት እንዲሁም በፈተናዎች ደህንነት ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
 
የ12ኛ ክፍል ፈተና ተጠናቆ የውጤት ትንተና ከተሰራ በኋላ በመጀመሪያው ዙር ከተሰጡት የትምህርት አይነቶች የሲቪክስ ትምህርት ፈተና እንደወጣ የሚያሳዩ አሳማኝ መረጃዎች መቅረባቸውን ተከትሎ የሲቪክስ ውጤት ከዩኒቨርሲቲ መቁረጫ ነጥብ እንዲሰረዝ መወሰኑን የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙዔል ክፍሌ ገልጸዋል።
 
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፈይሳ በበኩላቸው÷ከክልሎች የተውጣጡ የፖለቲካ አመራሮችና የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት የውጤት ትንተና እና የአስተራረም ሂደት ታይቶ የተፈጠረ ምንም አይነት ችግር እንዳልነበረ ግልጽነት ተፈጥሯል ብለዋል።
 
በፈተና እርማትና ውጤት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ያለበት ማንኛውም አካል ሂደቱን ለመፈተሽና ለማረጋገጥ ከፈለገ አሁንም ቢሆን ማስተናገድና ግልጽነት መፍጠር እንደሚቻል አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ መግለጻቸውን ከምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.