Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ከንቲባዎች ለ1 ሺህ 443ኛው የረመዳን ፆም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ለ1 ሺህ 443ኛው የታላቁ የረመዳን ፆም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 443ኛው ታላቁ የረመዳን ፆም በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

በረመዳን ወር ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የመደጋገፍ ባህሉን ከምንጊዜውም በላይ እንዲያጠናክር አብሮነትን፣ ወንድማማችነትንና ሰላምን በማጠናከር ማሳለፍ ይገባል ነው ያሉት።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ ለረመዳን ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ጾሙን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና በማሰብ መሆን ማሳለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመልእክታቸው ለመላው የእስልምና ተከታዮች በተለይ ለኢትዮጵያውያን እንኳን ለ1ሺህ 443 ኛው የረመዳን ፆም ወቅት አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን ይህ ታላቅና የተባረከ ወር በልዩ ሁኔታ ከአላህ ጋ የምንገናኝበት እና በዱአ ለሀገርና ለህዝባችን ሰላም፣ እድገት፣ መረጋጋትና የተሻለ ነገር የምንመኝበት ወቅት ነው ብለዋል።

ረመዳን የመልካምነት ፣ የንስሃ ፣ የይቅርታ ፣ የተቸገሩትን የመርዳት እና የሌሎች ብዙ ፀጋዎች ወር ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ በዚህ የፆም ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን ማስታወስና ከጎናቸው መቆምን መዘንጋት እንደማይገባም አመላክተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ይህን የተከበረ እና የተባረከ ወር በፆም እና በዱአ ሲያሳልፍ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በማስታወስ መደገፍና በዱአውም ማሰብ አለበት ነው ያሉት በመልእክታቸው።

ፆሙ ሰላም፣ መተባበር ፍቅርና አንድነት የሚጎለብትበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለረመዳን ጾም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክጅታቸው ረመዳን የበጎ ነገሮች ሁሉ ወር በመሆኑ ይቅርታ የሚያብብበት ፣ ሰላምና መተሳሰብ የሚጎላብትበት ፣ ስለሃገራችን ስለህዝባችን የሚፀለይበት ፣ አንድነታችን የሚጠነክርበት ፣ የደከሙት የሚደገፉበት ፣ ያዘኑት የሚፅናኑበት ፣ ካለን የምናካፍልበት ፣ የታረዙት የሚለብሱበት ፣ ማዕዳችንን የምናቋድስበት ፣ በረከቱ ለሁላችን የሚደርስበት መልካም የፆም ወር እንዲሆን ተመኝተዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.